የቱርክ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ቢዝነስ መድረክ ተካሄደ

1424

ቱርክ ጥቅምት1/2011 የቱርክ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ቢዝነስ መድረክ በአፍሪካና ቱርክ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ሚና እንደሚኖረው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በቱርክ ኢስታንቡል እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የቱርክ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ቢዝነስ መድረክ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል።

በዚህም መድረኩ በአፍሪካና ቱርክ መካከል ያለውን የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማሽጋገር ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ቱርክ በአፍሪካ ያላት እንቅስቃሴ በአፍሪካ ሀገሮች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ መሆኑን ገልጸዋል ።

ፕሬዚዳንቱ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በቱርክ ኢስታንቡል ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ ከ150 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ያህል መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ 30 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በበርካታ የቢዝነስ አማራጮች ላይ የሚያደርጉትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ንግድና ኢንቨስትመንት የቱርክ -አፍሪካ ስልታዊ ትብብር ምሰሶዎች መሆናቸውንም አውስተዋል።

መድረኩ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፣ በቱርክ የንግድ ሚኒስቴርና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ቦርድ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።