የአፋር ሕዝብ ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ ስርአት "ዳጉ" በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው

135
ሰመራ ጥቅምት 1/2011 የአፋር ሕዝብ ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ ስርአት የሆነውን "ዳጉ" በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የባህል ሃብትና ቅርስ ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃቢብ መሀመድ በክልሉ ለሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ተገቢውን ጥበቃና አንክብካቤ በማድረግ ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው። ከቅርሶቹ መካከል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ጥንታዊ መስጊዶች፣ የአውሳ ሱልጣኔት ቤተመንግስት፣ የአፋር ሀዝብ ለረጅም ጊዜ ራሱን በራሱ ያስተዳደረባቸው ባህላዊ ህጎችና የመረጃ መለዋወጫ ስርአቱ- ዳጉ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ "ዳጉ" ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ ስርአት ሕብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ የተከሰቱ ሁኔታዎችንና ወቅታዊ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ይህም አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ራሱንና አካባቢውን ከአደጋ የሚጠብቅበት፣ ልማቱን የማያፋጥንበትና ማህበራዊ ትስስሩን የሚያጎለብትበት ክዋኔ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። አቶ ሃቢብ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማህብራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ያልተረጋጋጡ መረጃዎች በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነትና ስነ ልቦና ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ። " በዳጉ የመረጃ ልውውጥ ስርአት ውስጥ አንድ ሰው ለሌላው መረጃ ሲያሰራጭ የመረጃ ምንጩን ጨምሮ የሚገልጽ በመሆኑ የተሰራጨው መረጃ እውነት ሁኖ ካልተገኘ መረጃውን ያስተላለፈው ሰው የሚቀጣበት አሰራር አለው፤ በእዚህም አስተማሪነቱን የጎላ ነው" ብለዋል። ይህን ድንቅ ባህላዊ ትውፊት ከቀድሞ በተሻለ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለእዚህም ቢሮው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። እስካሁንም ዓለም አቀፍ የዘርፉን አጥኚዎችና ተመራማሪዎች ለመሳብ በዳጉ ላይ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎችን እንዲሁም ዳጉ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚ ልማት ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ መሰራቱንም ዳይሬክተሩ አቶ ሃቢብ ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም