በሞጆ ደረቅ ወደብ የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት የዲዛይን ጥናት በመጠናቀቅ ላይ ነው

91
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 ሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ  ፕሮጀክት የዲዛይን ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ አስመጪዎች፣ ላኪዎችና የተለያዩ ደንበኞች በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚደርስባቸውን መጉላላት ለመቀነስ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከልን ሊገነባ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ባለስልጣኑ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ሐምሌ 2017 ከዓለም ባንክ የዲዛይን ፈቃድ አግኝቶ በመጀመሪያ የዲዛይን ጥናቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው። በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ  ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዶክተር መንግስት ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ግንባታው የሚከናወነው ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ነው። ግንባታው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2022 እንደሚጠናቀቅና የዲዛይን ጥናቱም በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በዲዛይን ጥናቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዓለም ባንክን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ይጀምራል ብለዋል። ግንባታው ሲጠናቀቅም በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ያለውን አሰራር ወደ ኤሌክትሮኒክስ በመቀየር ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ዘመናዊ አሰራር ይኖረዋል ነው ያሉት። የሞጆ ደረቅ ወደብ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት፣ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የተሟላ የኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል። በመሆኑም የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት እነዚሀን ችግሮች በዘመናዊና በተቀናጀ መንገድ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም