በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልተሰራበት ተገለጸ

74
አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልተሰራበት ተገለጸ። እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ቱሪስቶች  ለሚጎበኟት አገር የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ወሳኝ ቢሆንም እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በሆቴል አገልግሎት ጥራት አገሪቷ በዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ደረጃ  ላይ መሆኗ ተገልጿል። ዘርፉ ያለበትን ክፍተት ለመሙላትም በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ በኮከብ ሆቴሎች ውስጥ በምግብ ማብሰል ለተሰማሩና ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በአዲስ አበባ መሰጠት ተጀምሯል። ስልጠናው የሚሰጠው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ልምድና ክህሎት ቀስመውው በመጡ ኢትዮጵያዊያን  ነው። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ስለሺ ግርማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ለአራት ዓመታት በተከታታይ በወጡ መረጃዎች መሰረት አገሪቷ በሆቴልና አገልግሎት ጥራት የመጨረሻዎቹ  ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም ባለመፈጠሩ በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ብዙ መሰራት አለበት ብለዋል። በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ መስተንግዶ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወርቁ  በበኩላቸው እንደገለፁት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ አቅምና ክህሎት ያስፈልጋል። በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የምግብ አሰራርና መስተንግዶ ለመስጠትም እንዲህ አይነት ስልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አሁን ባለው ሁኔታም ችግሮቹን በመገንዘብ ዘርፉን ለማሳደግ የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋምና የሼፍ ማህበር  በርካታ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ሲሆኑ እንዲህ ያሉ ከመደበኛው ትምህርት ውጪ የሚዘጋጁ ስልጠናዎችም ዘርፉን ለማገዝ  ይጠቅማሉ። በተግባር  የተደገፉ ስልጠናዎች ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋልም ተብሏል። ሰልጣኞቹ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በተሰጣቸው ባለኮከብ ሆቴሎች ውስጥ በዋና ምግብ አዘጋጅነት የሚያገለግሉና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም አሰልጣኞች ናቸው። ስልጠናው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ሲሆን ለተከታታይ 16 ቀናት የሚዘልቅ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም