በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ተናቦ አለመስራት በተያዘው ግብ ልክ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል

67
አዲስ አበባ ጥቅምት1/2011 በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ተናቦ አለመስራት ዘርፉ በታቀደው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጓል ተባለ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው። ለዚህም መንግስት ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች የሚስቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ወጪ ንግድ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል። ነገር ግን በኃይልና በሎጅስቲክ አቅርቦት፣ በውሃ አቅርቦትና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በሌሎች መሰረተ ልማትን ለማቅረብ ሃላፊነት ባለባቸው ተቋማት መካከል ተናቦ መስራት አይስተዋልም ብለዋል። እነዚህ ተቋማት እስካሁን ባለው ሂደት ለየቅል እየፈጸሙ  ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን በመካከላቸው የተቀናጀ እቅድ ባለመኖሩ ምክንያትም በሚፈለገው መጠን ውጤታማ አልሆኑም። ግንባታቸው የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ መሰረተ ልማት በጊዜ አለመቅረብና ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር በተቋማቱ ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ናቸው። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውስጥ መሰረተ ልማትና ሌሎችን በማቅረብ ሃላፊነት ባለባቸው ተቋማት መካከል የመረጃ፣ የመናበብ፣ የተቀናጀ እቅድና ቋሚ የምክክር መድረክ አለመኖርም ዘርፉን በሚፈለገው ርቀት አንዳይሄድ አድርጎታል። "ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት ብቻውን ዋጋ የለውም" የሚሉት ስራ አስፈጻሚዋ፤ "መደመር በፍቅር ብቻ ሳይሆን በስራና በዓላማ ሊሆን ይገባል" ሲሉም አጽእኖት ሰጥተዋል። የአውደ ጥናቱ ዓላማም እስካሁን በተሄደው ርቀት በተለይም ሁሉም የራሱን እቅድ በማውጣት በራሱ የፈጸመበት አካሄድ ብዙ ርቀት ሊያስኬደን ስለማይችል ተናቦ መስራት የሚቻልባቸውን አካሄዶች ለማስቀመጥ ነው ብለዋል። እያንዳንዱ ተቋም የተነሱ ችግሮችን  ወደ ራሱ ወስዶ በማየት በተያዘው በጀት ዓመት ለውጤታማ ስራ አንረባረብ በማለትም ጥሪ አቅርበዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚታደርገው ጉዞ እውን እንዲሆን የዘርፉ ተዋናዮች ተናበው መስራት ወሳኝ መሆኑን በአትኩሮት አንስተዋል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዜጎች የስራ አድል በመፍጠር በኩልም ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩልም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸውያሉት ዶክተር አምባቸው፤  ይህ የሚሆነው ግን ሁሉም የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሲወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ወደ ስራ የገቡ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘው በጀት ዓመት በሙሉ አቅም ማምረት እንደሚጀምሩም ተናግረዋል። የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ አስገዶም እንዳሉት ቦሌ ለሚ አንድ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ የገቡ ናቸው። እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ባለው ሁኔታ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ስላልተሟሉላቸው በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አልነበረም። በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት ኢንቨስተሮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና ሙሉ የሰው ሃይል እንዲኖር መሰረተ ልማት እንዲሟላ ይደረጋል ብለዋል። እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለጻ ለአራቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስፈላጊዎቹ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ለማድረግም ስራዎች እየተከናወኑ ነው። የአሜሪካ፣ የህንድ፣ቻይና፣ ሲሪላንካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኮሪያ እና የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከገቡ ባለሃብቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ዛሬ እየተካሄደ ባለው አውደ ጥናትም በትራንስፖርት፣ ውሃና መብራት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ትምህርትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጽንሰ ሃሳብ መታወቅ የጀመረው ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ሲሆን እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም