ፍኖተ ካርታው በትምህርት ጥራትና በምርምር ስራዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል - የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን

51
ሐረር ጥቅምት 1/2011 ረቂቅ የትምህርትና ስልጠና  ፍኖተ ካርታ በትምህርት ጥራትና በምርምር ስራዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን እንደሚቀርፍ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ። መምህራኑ በትምህርት ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ላይ ያካሄዱትን ውይይት አጠናቀዋል፡፡ መምህራኑ በተለይ በትምህርት ጥራት፣ በመምህራን ጥቅማጥቅም፣ በምርምር ኢንደስትሪ ትስስር እና በሌሎች ስራዎች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን አንስተው ውይይት አድርገዋል። ፍኖተ ካርታው በትምህርት ጥራትና በምርምር ስራዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ  መሰረት አድርጎ የተቃኘ በመሆኑ በትምህርት ጥራና በምርምር ስራዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን እንደሚቀርፍ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪና መምህር ዶክተር ቦሰና ተገኝ ገልፀዋል፡፡ ''ፍኖተ ካርታው በተለይ  በመደርደሪያ ላይ ብቻ የሚቀሩት የምርምር ስራዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ያግዛል'' ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ መምሀር ተባባሪ ፕሮፌሰር ገመቹ አበራ በበኩላቸው በፍኖተ ካርታው የቀረበው የትምህርት አካሄድ በእውቀትም ሆነ ስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት መምህራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ የፈተናና የምዘና ስርዓቱ ከትምህርት ሚኒስትር ውጭ ገለልተኛ እንዲሆን የተቀመጠው ነጥብ በትምህርት ጥራቱና በምርምር ስራዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በመምህራን ምልመላ፣ ምደባና ቆይታም ፍኖተ ካርታ ያስቀመጠው አካሄድ የሚበረታታ ቢሆንም በደሞዝና በጥቅማ ጥቅም ላይ ዘርዘር ያለ ነገር መቀመጥ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ የዪኒቨርሲቲው የእንሰሳት ህክምና ኮሌጅ ተባባሪ ዲን ዶክተር ተስፋህይወት ዘሪሁን  እንደገለፁት መምህራን  ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከግብዓት አቅርቦት እስከ አደረጃጀትና አመራር ምን መሆን እንደሚገባ የውይይታቸው ትኩረት እንደነበር ገልፀዋል። በተለይም  በአሁኑ ወቅት በትምህርት ስራ አቅጣጫየውጭ አገራት ተሞክሮን አቅምንና ባህልን በአማከለ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው አሰራሮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ  በውይይቱ መምህራኑ ለረቂቅ የትምህርት ለፍኖተ ካርታው ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦችና መፍትሄዎች አቅርበዋል። በውይይታቸውም በተለይ በዩኒቨርስቲ መምህራን መቆያ ጊዜ እና ጥቅማ ጥቅም፣ በችግር ፈቺ የምርምር ስራ፣ በትምህርት ጥራት፣ በትምህርት ግበዓት አቅርቦት በፈተናና ምዘና፣ በማህበረሰብ አገልግሎት ስራና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተዋል። የተነሱ ሃሳቦችን ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርብ ዶክተር ጀማል ተናግረዋል። ለሶስት ቀናት በተካሄደው ውይይት በዋናው ግቢ እና ሐረር ከተማ በሚገኘው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ ከ900 በላይ መምህራን በቡድንና በጋራ ውይይት በማድረግ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም