የአሶሳ ነዋሪዎች ትችት

93
በሲሳይ ማሞ /ኢዜአ/ ሰሞኑን “የብዝሃነት አያያዝ፣ የፌደራሊዝም ስርዓትና ህገ-መንግስቱ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሔዶአል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎች የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የክልል ምክር ቤት አባላትና የሃይማኖት አባቶች ይገኙበታል፡፡ መድረኩ ያዘጋጁት  ደግሞ የፌዴሬሽንና የክልሉ ምክር ቤት ናቸው፡፡ ለውይይት የቀረበውን መነሻ ሃሳብ ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች የፌደራልና የክልሉ ህገ-መንግስቶችን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በግልጽ ተችተዋል፡፡ በአንጻሩ ህገ-መንግስቶቹን የሚደግፉ ሃሳቦችም ከተሳታፊዎቹ በስፋት ተንሸራሽረዋል፡፡ ጠንካራ ትችት ካቀረቡት ተሳታፊዎች መካከል የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁር አቶ አዳሙ ጅባት ይገኙበታል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደተናገሩት በቅርቡ የተጀመረው ሀገራዊ የመደመር ጉዞ በህገ-መንግስቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚንፀባረቁ ሁለት ጽንፈኛ ሀሳቦች አሉ ። በአንድ ወገን “ ብሄርን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም ይቅር ” የሚል ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ “ መደመር በህገ-መንግስቱ እውቅና ያገኘውን ማንነት የሚጨፈልቅ ነው” የሚሉ ሃሳቦች ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ ሃሳቦች መደመር ልዩነትን ጨፍልቆ አንድ ቋንቋና ብሄር መገንባት ሳይሆን ተቻችሎና ተከብባሮ አገር መገንባት እንደሆነ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ አለመሠራቱን ያሳያል ሲሉ አስተያየት ሰጪው ይጠቁማሉ፡፡ “ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ” ያሉት አስተየት ሰጪው ሆኖም “ ስርዓቱ ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ ነው ብሎ ማመን ደግሞ አደጋ ሊኖረው ይችላል ” በሚል የራሳቸውን እይታ አስቀምጠዋል፡፡ በፌዴሬሽን እኩል ስምምነት የፈጠሩ በሃገሪቱ የሚገኙ ክልሎች መካከል እኩል የመልማት ዕድል ካልተፈጠረ ለሀገር ፈታኝ ጉዳይ እንደሆነ አቶ አዳሙ ያሰምሩበታል ። የክልሎች ግንኙነት የጋራ ጥቅምና መከባበር መሠረት በማድረግ የአንዱ መጎዳት የሌላው ህመም መሆኑን ግንዛቤ ካልተያዘ ሀገራዊ ጫና ያስከትላል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ለዚህ እንደማሳያ የጠቀሱት ደግሞ ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ጉዳይ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ አሁንም ጥልቅ ውይይት የሚፈልጉ በርካታ አንቀጾች አሉት ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የህግ ባለሙያው አቶ አለባቸው ጊዳ ደግሞ በህገ-መንግስቱ የሚገኘው “ ነባር ብሄረሰቦች ” የሚለው ቃል ብቻ በመመልከት ነባሩ ብሔረሰብ የተለየ ተጠቃሚ የሆነ በማስመሠል ትርጉም እየተሰጠው ይገኛል የሚል ሀሳብ አንቀጸባርቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደእርሳቸው አገላለጽ የክልሉ ነባር ብሄረሰቦች በተግባር በሚገባ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ ጉዳዩ ተጨማሪ ጥናት ተደርጎበት ችግሩን ከነመፍትሄው በበለጠ ማሳየት ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣይ የሃገሪቱ ምሁራን የቤት ሥራ እንደሆነ እኚሁ ተሳታፊ መክረዋል፡፡ አቶ ካሳሁን ኪዳኔ የተባሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑ ሌላው ህገ-መንግስቱን የተቹ ተሳታፊ ናቸው፡፡ “ የህገ-መንግስት አፈጻጸም ሲነሳ ራሳችንን ከሌሎች ክልሎች መወዳደር ሳይሆን እንደአንድ የሀገር አካል ለአፈጻጸሙ ምን አስተዋጽኦ አበርክተናል የሚለውን ማስቀደም ወሳኝ ጉዳይ ነው ” ይላሉ፡፡ “ህገ-መንግስት ቋሚ ነው” በሚለው ሀሳብ እንደማይስማሙ ተናግረዋል፡፡ እንደማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ደረጃ መሻሻል እንዳለበት በመጥቀስ፡፡ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠው “ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በተግባር ሲታይ ግን ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን ለራስ መገልገያ ሆኖአል” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በሀገራችን ህገ-መንግስት በተግባር አልዋለም የሚሉት አቶ ካሳሁን “ ህጉ ቢተገበርማ ኖሮ በጠራራ ጸሐይ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ባልተገደሉና ባልተፈናቀሉ ነበር ። ፍትሃዊ የሃብት ከፍፍልም ይረጋገጥ ነበር  “  በሚል ተችተዋል፡፡ ለዚህ ተጠያቂ የሆነውን አካል በመለየት መፍትሄ ማምጣት አለብን ብለዋል፡፡ በአንጻሩ ህገ-መንግስቱን “ ምንም እንከን የማይወጣው አልማዝ ነው ” በሚል አጭር ቃል ያሞካሹት ደግሞ አቶ ጣሰው ጀጎ የተባሉ ተሳታፊ ናቸው፡፡ አቶ ሃሊድ አቡቤዳ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ደግሞ “ አመራሩ ህገ-መንግስቱን ለማስፈጸም አለመስራቱን የህገ-መንግስቱ አለመሟላት አድርጎ መተቸት አይገባም ” የሚል ሃሳብ በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ህገ-መንግስት ሲጣስ እርምጃ መውሰድ በቀጣይ ተግባራዊ መሆን ያለበት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ አቶ ዘላለም ጃለታ የተባሉ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ደግሞ የፌደራሉ ህገ-መንግስት ዜጎች በመረጡት የሃገሪቱ ሥፍራ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብት እንደሰጠ ያስታውሳሉ፡፡  ሆኖም ይህ አንቀጽ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጎምበት ወቅት አለ ብለዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በክልሉ ህገ-መንግስት ላይ ጥያቄ መነሳት የጀመረው የመሬት ኢንቨስትመንት እየተጠናከረ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ “ ወደ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ገብተው የተፈጥሮ ህብት የሚያወድሙ አሉ ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው “ አንዳንዶች በክልሉ ህገ-ወጥነት ለማስቆም የሚደረገውን ሂደት ከዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ጋር ለመቀላቀል ይሞክራሉ ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ብሄርን መሠረት አድርገን የቀረጽነው ህገ-መንግስት እስካልተሻሻለና እስካልተቀየረ ድረስ በዚሁ መመራት ግድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ የክልሉ ህገ-መንግስት ከሌሎች ክልሎች በተሻለ የክልሉን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የሀገሪቱን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ አግላይ አይደለም ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የግጭት አፈታትና የንቃተህገ-መንግስት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ በህገ-መንግስቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ብዝሃነት በማስተናገድ ረገድ ስኬቶች ቢኖሩም በርካታ የአፈጻጸም ችግሮች እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡ “ህገ-መንግስቱ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገን የደረስንበትን የእድገት ደረጃ ተከትለን ስናሻሻለው ነው ” ብለዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውይይቶች በአንዳንድ የህገ-መንግስቱ አንቀጾች ላይ አለመስማማት ይነሳል ይላሉ ዳይሬክተሩ፡፡ አቶ አስቻለው እነኚህ አከራካሪ አንቀጾች ጸድቀው ተግባራዊ የሆኑት በወቅቱ ብዙሃኑ ህዝብ ስለተስማማባቸው እንደሆነ ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት፣ የመንግስት ሥልጣን፣ በብዝሃነት አያያዝ፣ ፍትሃዊ ውክልና እና ተጠቃሚነት፣ የአማርኛ እና የኢንግሊዝኛ ትርጓሜው፣ የክልሎች ወሰን አከላለል፣ ሥልጣንን ወደ ህብረተሰቡ ማውረድ እና ሌሎችም በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚነሳባቸው የህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ይዘረዝራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በተለይም አሁን ካለው ሀገራዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ “ ብሔረሰብ ” እና “ኢትዮጵያዊነት” በሚል እየተነሳው ያለው ሃሳብ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ አልሆነም በሚለው ሃሳብ እንደሚስማሙ ተናግረዋል፡፡ የግንዛቤ ማነስ፣ ትኩረት ማጣት፣ የአመለካከት፣ የአቅም ማነስና ሌሎችም ችግሮችን ለህገ-መንግስቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመሆን ዳይሬክተሩ በምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡ “ በታዩት ክፍተቶች ላይ ህዝቡ ባሳተፈ መልኩ ህገ-መንግስቱን ለማሻሻል ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ” ሲሉ አቶ አስቻለው ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሙለታ ወምበር የክልሉ ህገ-መንግስት በክልሉ የሚኖሩ ሁሉንም ማህበረሰቦች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የተቀረጸ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የአፈጻጸም ድክመቶች እንዳሉ እርሳቸውም ይስማሙበታል፡፡ ዋና አፈ-ጉባኤው “ በህገ-መንግስቱ ላይ የሚነሱ ማናቸውም ሃሳቦች ላይ መወያየት እንጂ ማግለል ተቀባይነት የሌለው ነው ” የሚል እምነት አላቸው፡፡ ምክር ቤቱ ህብረተሰቡ በህገ-መንግስቱ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፍ ሙሁራንን ማሳተፍ ደግሞ በቀጣይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም