በትግራይ ክልል ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ እየተሰራ ነው

90
መቀሌ መስከረም 30/2011  ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ቁጥር ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከጤና ተቋማት ውጭ የሚወልዱ ነፍሰጡር እናቶችን ቁጥር ወደ ዜሮ ለማውረድ እተየሰራ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡ በትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ንዑስ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ከበደ አምባዬ እንዳሉት ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋም በባለሙያዎች ታግዘው እንዲወልዱ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለእዚህም 980 ለሚሆኑ አዲስና ነባር አወላጆች ተጨማሪ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠና መስጠቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በሁሉም የክልሉ ገጠር አካባቢዎች ቤት ለቤት በመሄድ ክትትል የሚያደርጉና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚሰጡ 749 ሺህ የጤና ልማት ቡድን አባላት አቅማቸው እንዲጎለብት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት ባለፈው ዓመት በክልሉ ከ162 ሺህ የሚበልጡ እናቶች በጤና ተቋማት በባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው እንዲወልዱ የተያዘው ዕቅድ 81 በመቶ ተሳክቷል፡፡ ያለጤና ባለሙያ ድጋፍ ቤታቸው ውስጥ ከወለዱ ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል 144ቱ ለህለፈተ ሕይወት መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ለእናቶቹ ሞት ምክንያት ከሆኑት መካከልም በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት የተከሰተ ደም መፍሰስ፣ የማህጸን ጥበትና በማህጸን ውስጥ የልጅ አቀማመጥ መዛባት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተያዘው የ2011 ዓመትም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ከ165 ሺህ በሚበልጡ ነፍሰጡር እናቶች ላይ የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኦፍላ ወረዳ የሀሸንገ  ቀበሌ ገበሬ ማህበር የጤና ልማት ቡዱን አባል ወይዘሮ ሃሪፈያ ሀጎስ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ነፍሰ ጡር እናቶች የቅድመና ድህረ ወሊድ ምርመራና ክትትል እንዲያደርጉ ቤት ለቤት በመሄድ ትምህርት መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል፡፡ "ሦስት ሴት ልጆቼ ጤና ተቋማት ሂደው እንዲወልዱ በማስተማር የቀበሌው ሞዴል የጤና ልማት ቡድን ሆኛለሁ" ያሉት ደግሞ በክልተ አውላዕሎ የአብረሃ ወአፅበሃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ተበርህ አሳየኸኝ ናቸው፡፡ በመቀሌ ከተማ አድሓ ጤና ጣቢያ የሚሰሩት ሲስተር ሰዓዳ ዓብደላ በጤና ቢሮው በኩል የሚሰጠው ስልጠና ከእዚህ በፊት በአቅም ማነስ ምክንያት ይከሰት የነበረውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡ በየቀኑ ከ15 እስከ 20 ለሚደርሱ ነፍሰጡር እናቶች የጤና ምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ሲስተር ሰዓዳ ገልጸዋል፡፡ በዓይደር ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ የሆኑት ሲስትር ፍረወይኒ ታደለ በበኩላቸው " በየቀበሌው ከሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር በመቀናጀት ነፍሰጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋም መጥተው እንዲወልዱ በቅንጀት እየሰራን " ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም