ከዞኑ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል

71
ሁመራ መስከረም 30/2011 ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን በ2010/11 የምርት ዘመን ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ገለጸ፡፡ ምርቱን ለመሰብሰብ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የቀን ሠራተኞች ወደ ዞኑ ገብተዋል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ተስፋይ የእብዮ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በምርት ዘመኑ ከቀዳሚው የምርት ዘመን በ100 ሺህ ኩንታል ብልጫ ነጭ የሁመራ ሰሊጥ ይገኛል ተብሎ ይገመታል። በዞኑ በዚህ የምርት ዘመን 282 ሺህ ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የክረምቱ የዝናብ ወቅት ለሰብል ተስማሚ ስርጭትና መጠን እንደነበረውም አስረድተዋል፡፡ ምርቱን በዘመቻ ለመሰብሰብ  ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ የቀን ሠራተኞች ወደ አካባቢው መግባታቸውን አቶ ተስፋይ አስረድተዋል፡፡ ምርቱን ለማሰባሰብ ከአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች የቀን ሠራተኞች ወደ አከባቢው መግባታቸውን የተናገሩት በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በሰሊጥ የእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብት አቶ ተክላይ ዘርአይ ናቸው፡፡ባለፈው ዓመት አጋጥሟቸው የነበረውን የሠራተኞች እጥረት መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቱ በ100 ሄክታር መሬት የዘሩትን ሰሊጥ የሚሰበስቡ በቂ የቀን ሠራተኞች መገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ ባለፈው አመት በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች በነበረው አለመረጋጋት የቀን ሠራተኞች እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ  አቶ ገብረህይወት የማነ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብት ናቸው፡፡ በዚያን ወቅት የቀን ሠራተኞች ከፍያ እስከ 400 ብር ደርሶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ የቀን ሠራተኞች ክፍያ ከአምናው በግማሽ በመቀነሱ ባለሀብቶችም ሆኑ የቀን ሠራተኞች ሳይጎዱ ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል። የቀን ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስ ሰርተው በገቢው እየተጠቀሙ ናቸው ብለዋል።᎐ ምርቱን ለመሰብሰብ ወደ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ የመጣው ወጣት ዘመንፈስ ዘለቀ ዘንድሮ በአገሪቱ በተፈጠረው የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ወደ አካባቢው መጥቼ ለመስራት ችያለሁ ብሏል፡፡የቀን ገቢው እስከ 200 ብር መድረሱንም ተናግሯል፡፡ ወጣት መስፍን አደራጀው የተባለ የቀን ሠራተኛ በበኩሉ በአገሪቱ የሰፈነው አንጻራዊ  ሰላምና መረጋጋት ወደ አካባቢው ሄዶ ለመሥራት እንዳስቻለው አስታውቋል፡፡ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ሰሊጥን ጨምሮ  ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም