በሃዋሳ ከተማ ለፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ ይሆናሉ....የከተማው አስተዳደር

93
ሃዋሳ መስከረም 30/2011 በሃዋሳ ከተማ ለመሰረተ ልማት ፕሮጅክቶች ግንባታ መጓተት ምክንያት የሆኑ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ አፋጣኝ ውሳኔ እንደሚሰጥ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ትናንት ባደረገው የመስክ ምልከታ በ700 ሚሊዮን ብር በመገንባት ላይ ያሉ ሰባት ፕሮጀክቶች መዘግየታቸውን አረጋግጧል ። የሃዋሳ ከተማ አስተዳዳር ምክትል ከንቲባ አቶ ሱኳሬ ሹዳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በሚገባቸው ጊዜና ውል መሰረት አልቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፡፡ የመንገድ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ግንባታ እንዲሁም የጎርፍ መውረጃ ቦይና የቱሪስት መረጃ ማሳራጫ ማዕከል ከኮንትራት አስተዳዳር ጋር በተያያዘ የዘገዩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከመንገድ ግንባታ አኳያ የዲዛይንና የወሰን ማካለል ለመዘግየቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው በመንግስት በኩልም በቂ ድጋፍና ክትትል አለመደረጉ ፕሮጀክቶቹ በውላቸው መሰረት እንዳይጠናቀቁ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ደረጃ ካቢኔው በመስክ ምልከታ ያረጋገጠ በመሆኑ አስተዳደራዊ ውሳኔ በማስተላለፍ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል፡፡ እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ መዘግየት የታየባቸው ሰባት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በ700 ሚሊዮን ብር የተጀመሩ ናቸው። "ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ከሚገባቸው ከአንድ እስከ አራት ዓመት ዘግይቷል" ያሉት ምክትል ከንቲባው ችግሩን በፈጠሩ ሥራ ተቋራጮች ላይ በውላቸው መሰረት ቅጣት እንደሚተላለፍ አስታውቀዋል፡፡ በከተማው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው የወጪ ቆጣቢ አዲስ የቤት ፕሮጅክት ግንባታ በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባው ተናግረው፣ የግንባታው ሥራው በሁለት ወር ውስጥ ተጠናቅቆ ቤቶቹ ለ156 ቤተሰቦች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል። የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ በበኩላቸው "ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት መሰረታዊ ችግር በመሰረተ ልማት ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ያለመቀናጅት ነው" ብለዋል። የመብራት ምሰሶዎች፣ የውሃና የስልክ መስመሮች ችግር መሆናቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል። "ማዘጋጃ ቤቱም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢ ካሳና ምትክ ቦታ ሰጥቶ ፈጥኖ ያለመፍታት ውስንነት አለበት" ሲሉም ገልጸዋል። ከዘገዩት ፕሮጀክቶች መካከል አራቱ የዲዛይንና የጥራት ችግር ያለባቸው መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ "ከጅምሩ ጠቃሚ መረጃዎችን ሰብስቦ የዲዛይን ሥራ በመስራት በኩል ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ በቀጣይ ውል በማቋረጥ ዲዛይኑን የማሻሻል ሥራ ይከናወናል" ብለዋል፡፡ "በተቋራጮች፣ በአማካሪው ድርጅትና በመንግስት አካላት በኩል ለህዝብ ወግኖ ያለመስራት ችግር መኖሩን ገምግመናል" ብለዋል አቶ ፍቅሩ፡፡ ተጨማሪ በጀት የሚጠይቁ ሥራዎች በመኖራቸው ከካቢኔው ጋር በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ስራስኪያጁ ጠቁመዋል። በከተማው በተደጋጋሚ በክረምት ወቅት የሚያስቸግረውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ስምንት ትልልቅ የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን ለማሰራት የአራት ፕሮጀክቶች ጨረታ ወጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም