የጋማ ከብቶቻችንን ከበሽታ የሚታደግ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም---የመንዝ ቅያ ገብርኤል ወረዳ አርሶ አደሮች

69
ደብረ ብርሃን መስከረም 30/2011 በአካባቢያቸው የተከሰተውን የጋማ ከብቶች በሽታ ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕክምና አገልግሎት ማጣታቸውን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ መንዝ ቅያ ገብርኤል ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። የዞኑ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ የበሽታውን መንስኤና መቆጣጠሪያ ዘዴ ለማወቅ በቤተ-ሙከራ የታገዘ የናሙና ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል። በመንዝ ቅያ ገብርኤል ወረዳ የአመጃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባሻው ከበደ ለኢዜአ እንደገለፁት ከመስከረም ወር 2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በአካባቢው በተከሰተ በሽታ አህያዮች፣ በቅሎዎችና ፈረሶች እየሞቱ ነው፡፡ በሽታው የጋማ ከብቶችን ሰውነት በማዛልና እንዳይመገቡ በመከልከል በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ለሞት እየዳረጋቸው መሆኑን ጠቁመዋል። "እኔም አንድ የጭነት አህያዬ ላይ የበሽታውን ምልክት በማየቴ ወደ ህክምና ተቋም ብወስደውም ከበሽታው ሊታደግ የሚችል መድህኒትም ሆነ ሕክምና ማግኘት ባለመቻሌ ሞቶብኛል" ብለዋል። አርሶ አደር ዳምጠው ፈለቀም  በበሽታው ሁለት አህዮችን በሞት ማጣታቸውን ተናግረዋል ። "በአህዮቹ ላይ የህመሙን ምልክት እንዳየሁ ወደ ህክምና ብወስዳቸውም መድኃኒት ሊሰጧቸው ባለመቻሏቸው ሞተውብኛል" ብለዋል። ለችግሩ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግላቸውም አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል። በወረዳው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር በላይነህ አያሌው በበኩላቸው በአካባቢው የተከሰተው በሽታ ምንነትና መንስኤ ባለመታወቁ ተጠቂ የሆኑትን የጋማ ከብቶችን ፈጥኖ በህክምና መታደግ አልተቻለም። ችግሩ ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ የደብረዘይት እንስሳት ምርምር ማዕከልና በፌደራል ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት መደረጉን ተናግረዋል። በሽታው እንዳይዛመት ህብረተሰቡ ጤናማ የጋማ ከብቶችን በበሽታው ከተጠቁት ለይቶ እንዲይዝ እየተደረገ ነው ብለዋል። የዞኑ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የእንስሳት በሽታ ቅኝት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዘላለም ይታየው በወረዳው በስምንት ቀበሌዎች በተከሰተው በሽታ እስካሁን ከተጠቁ 62 የጋማ ከብቶች ውስጥ 45ቱ መሞታቸውን ተናግረዋል። የበሽታውን ምንነትና መንስኤ እንዲሁም የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ለማወቅ በኮምቦልቻ እንስሳት ቅኝት ጥናትና ላቦራቶሪ ማዕከል አማካኝነት ከተጠቂ የጋማ ከብቶች ናሙና ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል። በክልልና በፌደራል ደረጃ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንዲያውቁት ተደርጎ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ባለሙያው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም