በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ለተገጩ እንስሳት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል

72
አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ለተገጩ እንስሳት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን የኢትዮጵያ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ገለጸ። በባቡር መስመሩ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችና የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅትና ህጎችንም መተግበር እንደሚገባም አመልክቷል። የማህበሩ የደህንነት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጥበበ ተረፈ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባቡሩ በሠዓት 120 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ቢኖረውም እየተጓዘ ያለው በሠዓት ከ70 ኪሎ ሜትር በታች ነው። ባቡሩ በአቅሙ ልክ እንዳይጓዝ በመስመሩ ላይ ያለው የአደጋ ተጋላጭነት ፈተና እንደሆነበትም ተናግረዋል። በእስካሁን የባቡሩ እንቅስቃሴም 370 እንስሳት ላይ አደጋ ደርሷል፤ ለዚህም ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ካሳ ተከፍሏል። በእንስሳት ላይ ከሚደርሰው ግጭት በተጨማሪም የባቡር ሃዲዱ ብሎኖች እየተሰረቁና የውድመት አደጋ እየደረሰ እንደሆነም ገልፀዋል። በባቡር መስመሩ ላይ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማነስና ህግና ደንቦችን የማስፈፀም ክፍተት መኖሩ አደጋው እንዲበራከት ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ማህበሩ አደጋዎችን ለመቀነስ ከኀብረተሰቡ ጋር ውይይት መጀመሩንና በማቋረጫዎች ላይ ሰራተኞች በመቅጠር የማስተባበርና የግንዛቤ መፍጠር ስራ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በቀጣይ የአደጋዎች ተቀዳሚ ምክንያት ነው ተብሎ የተለየውን የግንዛቤ ማነስ ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ውይይቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል ታቅዷል ብለዋል። ማቋረጫዎቹ በርካታ በመሆናቸው ከኀብረተሰቡ ጋር በመነጋገር በግማሽ ያህል ለመቀነስ እንዲሁም ተደጋጋሚ አደጋ ደርሶባቸዋል ተብለው በተለዩ መስመሮች ላይ አጥር የማጠር ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል። ስርቆትና አደጋዎችን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት ከማህበሩ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩና ህግና ደንቦች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ኀብረተሰቡም የባቡር መስመሩ ጠቀሜታ ለእሱም መሆኑን ተረድቶ መሰረተ ልማቱን መጠበቅ፣ መንከባከብና ከስርቆትና ውድመት መከላከል እንደሚገባውም አሳስበዋል። የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እቃና ሰዎችን የማጓጓዝ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም