በኢትዮጵያ ከህመም ነጻ የህክምና ተቋም ኢኒሼትቭ አበረታች ውጤት እየተገኘበት ነው-ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

62
አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 በኢትዮጵያ ከህመም ነጻ የህክምና ተቋም ኢኒሼትቭ አበረታች ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ። የህመም ስቃይ ማስታገስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ በመስኩ የተለያዩ ሆስፒታሎች ያገኙት ውጤት ምን ይመስላል? በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል። ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው መድረክ ላይ በዘርፉ የሚሰሩ መንግታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኪሊኒካል አገልግሎት ዘርፍ ተወካይ ወይዘሮ ገነት ንጉሴ እንደሚሉት ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ሲመጡ ባለሙያዎች በቅድሚያ ትኩረት የሚያደርጉት በሽታውን ለይቶ ማዳን ላይ እንጂ ህመምን ማስታገስ ላይ አይደለም። ችግሩን ለማቃለልም እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ ኢኒሼቲቩ ተቀርጾ ሲተገበር መቆየቱን አንስተዋል። በዚህም በአገሪቷ የህመም ማከሚያ መመሪያ ማዘጋጀትና በጤና ተቋማት የስልጠና ማዕከላት በኩል ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠት ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል። የህመም ማስታገሻ  መድሃኒት አቅርቦትና ህመምን መለካት በኢኒሼቲቩ የተካናወኑ ሌሎች ተግባራት ናቸው። ወይዘሮ ገነት እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በ17 ሆስፒታሎች ታካሚዎች ቢድኑም ባይድኑም የህመም ማገገሚያ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው ለ3 ሺህ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል። በአገሪቷ 60 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች መካከለኛና ከፍተኛ ህመም ይሰማቸዋል፤ በተለይ ካንሰርና የልብ በሽታ ተጠቂዎች የመሳሰሉ ከፍተኛ የህመም ስሜት እንደሚሰማቸው አስረድተዋል። ኢኒሼቴቩ መተግበር ከጀመረ ጀምሮ 36 በመቶ ከፍተኛ ህመም ላይ የነበረው ወደ 13 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን መካከለኛ ህመም ላይ ደግሞ ከ 25 በመቶ ወደ 18 በመቶ ዝቅ ማለቱን ለአብነት ጠቅሰዋል። ''ህመምን ማስታገስ ትኩረት ተሰጥቶት አይሰራም ነበር'' ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል ናቸው። ሚኒስቴሩ ለባለሙያዎች ግንዛቤን ከመስጠት ባለፈ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ሞርፊንና ኮዲንን የመሳሰሉ ማስታገሻ መድሃኒቶች ለሆኖስፒታሎች ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ ታካሚው ስቃይ አለው ወይ? ደረጃውስ ምን ያህል ነው? የሚለውን በመለየት ድጋፍ በማድረግ ረገድም በመመሪያ የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በቀጣይም በሁሉም ሆስፒታሎች ኢኒሼቲቩን በመተግበር ለውጤታማነቱ ይሰራል ነው ያሉት። የህመም ማስታገስ አገልግሎት በስርዓተ ትምህርት ተካቶ ለህክምና ተማሪዎች እንዲሰጥም እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። ከ 65 ዓመት በላይ የሚሆኑ አረጋዊያንን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሆነም ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም