በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ተመዝጋቢዎችን ቁጥር ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ነው

84
ባህር ዳር መስከረም 30/2011 በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ተመዝጋቢዎችን ቁጥር ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አረጋ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ዜጎች በሰነድ የተረጋገጠ መረጃ እንዲኖራቸው ለማስቻል ምዝገባው እየተካሄደ ነው። ቀደም ሲል በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሉ የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ ለፍትህ ሥርዓት መጓደልና ኢ-ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ማድረጉን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት የዜጎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መዋቅር መዘርጋቱንና ባለፉት ሁለት ዓመታት የ520 ሺህ 700 ዜጎች ኩነቶች ምዝገባ መከናወኑን አቶ አረጋ አስረድተዋል። በዚህ ዓመትም 479 ሺህ 300 ኩነቶችን ለመመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በኩነቶቹ ከሚመዘገቡት መካከልም ልደት፣ሞት፣ፍቺ፣ጋብቻ፣ጉዲፊቻና አባትነትን መቀበል እንደሚገኙበት ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። ዕቅዱን ለማሳካትም ለባለሙያዎች ስልጠና ለኅብረተሰቡ ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚያገለግሉ ቋሚ ሰነዶችም በየደረጃው በተቋቋሙ ቅርንጫፎች መሰራጨታቸውን አቶ አረጋ ገልጸዋል። የልደት ኩነት አስመዝጋቢው አቶ ትዕዛዙ ተዋበ እንደገለጹት ምዝገባው በሞትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆች የተለያዩ  ልጆች ትክክለኛ  የወላጆቻቸውን ማንነት ለማወቅ ያስችላቸዋል ብለዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቀኑ ሳያልፍ እያስመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምዝገባው በእውነተኛ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ለመብቱ የሚታገል ዜጋ ከማፍራት ባለፈ በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ ያስችላል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሄለን ሃብቴ ናቸው። ሆኖም የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ ጥቅም ግልጽ አድርጎ ከማስረዳት አኳያ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ብለዋል። ኤጀንሲው  ምዝገባው የሚያስገኘውን ጥቅም ለተመዝጋቢዎች በማስገንዘብ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል። የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በአገርም ሆነ በክልል ደረጃ ከ2008 መጨረሻ ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም