የኮንስትራክሽን ዘርፍ አገራዊ አቅም በመገንባት ለኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

623

አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 የኮንስትራክሽን ዘርፉ አገራዊ አቅም በመገንባት ለኢኮኖሚው ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆየውን 9ኛውን ‘አዲስ ቢውልደር’ የኮንስትራክሽን ግብዓትና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከፍተዋል።

አቶ ደመቀ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሃገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱን አስታዋጽኦ እንዲያበረክት በአገራዊ አቅም ላይ መስራት ይገባል።

በዘርፉ በርካታ ተዋናዮች በተለይም ገንቢዎች፣ አልሚዎች፣ የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች፣ የሥራ ተቋራጮችና ሌሎችም የሚሳተፉበት ከፍተኛ የኢከኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል ነው ብለዋል።

ዘርፉ ከሌብነትና ከብልሹ አሰራር የጸዳ እንዲሆን፣ በጥራትና በተወዳዳሪነት እንዲሊቅ እንዲሁ ለትውልድ የሚተርፍ አገራዊ አቅምና ዘመናዊ አሰራር እውን ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠት እነደሚገባም አሳስበዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለስራ ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲውልና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲኖረውም መንግስት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በመስኩ ቀደምት ባለታርኮች ለአጋሪቷ መኩሪያ፣ መመኪያ የሆኑ ትውልድ ተሻጋሪ ቅርሶችን መገንባት እንደቻሉ ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ለትውልድ የሚተርፍ የግንባታ ስራ ለማከናወን አገራዊ አቅምን ለማጎልበት መትጋት ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው፤ አውደ ርዕዩ በመነቃቃት ላይ ያለውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት ለማረጋገጥና በሰው ሃይል ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፉ የግሉ ዘርፍ ትብብር የሚያደርግበትንና የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት መስራት እንዲቻልም ነው ሲሉ አክለዋል።

በኢግዚቢሽኑ በሳይንስዊ ጥናት ውጤቶች ላይ ፓናል ውይይቶች ማድረግ፣ ልምድ ማካፈል፣ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ አምራችና ገዥን ለገናኘት እንዲሁም በተፎካካሪ የንግድ ድርጅቶች መካከል ጤናማ ተነሳሽነትና ሰላማዊ የፉክክር ስሜት ለመፍጠር መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢግዚቢሽኑ ዘንድሮ ሲካሄድ ለ9ኛ ጊዜ ሲሆን በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ከቻይና፣ከግሪክ፣ከጣሊያን፣ከቱርክና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የመጡ ከ80 በላይ ተሳታፊዎች እየተሳተፉ ነው።