በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ2 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እየተሰራ ነው

77
ሰቆጣ መስከረም 30/2011 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ2 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ አዳነ ለኢዜአ እንደገለፁት በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ክፍተት በመስኖ ለመደገፍ እየተሰራ ነው። ልማቱ የሚካሄደው የክረምት የዝናብ ውሃን በማሰባሰብና የወንዝ ውሃን በዘመናዊ መንገድ በመጥለፍ እንደሆነም ተናግረዋል። በዚህ የበጋ ወቅት ከሚለማው ሁለት ሺህ 764 ሄክታር ውስጥ 525 ሄክታሩ በአዲስ የሚለማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ልማቱን ለማካሄድ በአሁኑ ወቅት ለ16 ሺህ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ስልጠናና የመሬት ልየታ ስራ እየተከናወነ ነው። በክረምቱ ወቅትም 21 ሺህ የማንጎ፣ አቦካዶና ሙዝ እንዲሁም አንድ ሺህ 422 የአፕል ፍራ ፍሬዎች በአርሶ አደሮች መተከላቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ከ50 ኩንታል በላይ የአትክልት ምርጥ ዘር እና 2ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን ገልፀዋል። ብሔረሰብ አስተዳደሩ ዝናብ አጠር አካባቢ እንደመሆኑ በበጋ ወራት በተለይ የሚስተዋለውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ 34 አነስተኛ ግድቦች ተገንብተው የውሃ አማራጭ በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ በምግብ እራሱን እንዲችል ለማድረግ ባለፉት ሁለት አመታትም 32 የወንዝ ጠለፋ ፕሮጀክቶችና የመስኖ ካናል ተገንብተው ከ2 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት መሰማራታቸውን አመላክተዋል፡፡ በሚለማው የመስኖ መሬትም ከአንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል። የዝቋላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ማርው ዝቋልሹም በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የሚገኘውን የጽጽቃ ወንዝን መሰረት በማድረግ በአንድ ሄክታር መሬት ማንጎ በማልማት በየዓመቱ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህ የበጋ ወቅት ለሚካሄደው የመስኖ ልማት ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልክተው የተሻለ ምርት በመሰብሰሰብም የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሰቆጣ ዙሪያ የ016 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዱኛው ንጉሱ በበኩላቸው በግማሽ በሄክታር መሬታቸው ቲማቲምና ሽንኩርት ምርት ለማምረት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አመት ቀይ ስርና ካሮት በማልማት ሁለት ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቀሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በዘንድሮው አመትም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችለውን 2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ዘርና 50 ኪሎ ግራም ማዳበሪያ ለመጠቀም ግዥ መፈፀማቸውን ተናግረዋል፡፡ በብሄረሰብ አስተዳደር ዞኑ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የመስኖ ልማት ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም