ለጨፌ ኦሮሚያ አዲስ ተሿሚዎች ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

57
ጊምቢ መስከረም 30/2011 ጨፌ ኦሮሚያ በቅርቡ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ለተሾሙ አዲስ አመራሮች ስኬታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ  እንዲያስቀጥሉ አዳዲስ ሰዎች ወደአመራርነት እንዲመጡ መደረጉ ጨፌው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በተሻለ ለማስፈጸም ያግዛል። ውሳኔዎቹ ተግባራዊ እንዲሆኑና ከግብ እንዲደርሱ አዳዲስ ተሿሚዎች ኃላፊነታቸው የጎላ መሆኑን አውቀው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ ለአመራሮቹ ውጤታማነት የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በጊምቢ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ዳንኤል ሞገስ እንዳሉት በጨፌው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችን እንዲመሩ የተሾሙት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በተሻለ ለመወጣት እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በአካባቢያቸው በተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞን ለማስቀጠል በሚከናወኑ ተግባራት ከመሳተፍ ጀምሮ ልማትን ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ባጫ ጉታ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከእዚህ ቀደም በተለያዩ የክልሉና የፌዴራል መንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩ ሰዎች መሾማቸው ለጨፌው ውሳኔዎች ተግባራዊነት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ጨፌ ኦሮሚያ ያካሄደው ሹመት የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያማከለ በመሆኑ አመራሮቹ የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራሉ ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መሰረት ይግዛው የተባሉ ነዋሪ ናቸው። ወጣት ሳሙኤል አዱኛ በበኩሉ ሹመቱ ብዙ የለውጥ አመራርን ያካተተ፣ በእውቀትና በሥራቸው ምስጉን የሆኑና በውጪ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር ማካተቱ የተለየ እንደሚያደርገው ተናግሯል። ተሿሚዎቹ በክልሉም ሆነ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላም፣ የዴሞክራሲና ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች በዜጎች ተሳትፎ እውን ለማድረግ ጠንክረው እንዲሰሩም ጠይቋል። በተለይ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማስጠበቅ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ የሚጠበቅበትን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል። የጨፌ ኦሮሚያ በቅርቡ ባካሄደው አራተኛ ዓመት ሦስተኛ አስቸኳይ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በተጨማሪ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ማጽደቁ ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም