አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ -ካርታ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም--- አንድ ምሁር

155
ባህር ዳር መስከረም 29/2011 አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም ሲሉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አንድ ምሁር ተናገሩ። የፍኖተ-ካርታው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የተነሳና የአደረጃጀት ግልጽነት ችግር የሌለበት መሆኑን የጥናት ቡድኑ ተወካይ አስታውቀዋል፡፡ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ገበዬሁ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት አዲሱ ፍኖተ-ካርታ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ያልተነሳና የሌሎች አገራት ፖሊሲን በመገልበጥ ለመተግበር የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፍኖተ-ካርታው ከእዚህ ቀደም የነበሩ መንግስታትን የትምህርት ፖሊሲዎች ጥንካሬና ክፍተት ካለመፈተሹ በላይ መነሻና መድረሻውን ባለፉት 20 ዓመታት ላይ ብቻ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል። ተቀጣሪም ሆነ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ምንም አይነት አስተዋጾ የሌላቸው የትምህርት አይነቶች በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ የጠቆሙት ምሁሩ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ይህንን የዳሰሰና ለዚህ መፍትሄ ያስቀመጠ አለመሆኑን ተናግረዋል። የፍኖተ-ካርታው የጥናት ቡድን አጋር ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታው ጥልቅ ጥናት የተደረገበት፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የተነሳና የአደረጃጀት ግልጽነት ችግር የሌለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የፍኖተ-ካርታው ተሞክሮ የተወሰደባቸው አገሮች በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የነበሩና በወሰዱት የፖሊሲ ለውጥ ከችግራቸው የወጡ ናቸው" ብለዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሚገኙ ግብአቶች የሚሻሻል መሆኑንም ዶክተር ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡ አዲሱ ፍኖተ- ካርታ አሁን እየተሰራበት ባለው የትምህርት ፖሊሲ ላይ በዘርፉ ምሁራን ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በዝርዝር የፈተሸና ዘላቂ መፍተሄ እንዲያመጣ ተደርጎ የተቀረፀ መሆኑንም ገልጸዋል። "በጥናቱ አሁን እየተሰራበት ባለው የትምህርት ፖሊሲ በዋነኛነት የሚስተዋሉ የግብረ ገብነትና የተግባር ተኮር ትምህርት ክፍተቶችን በመለየት ማስተካከልና ወደ ውጤታማነት መቀየር የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል" ብለዋል። ተማሪዎች በክህሎት የዳበሩና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ መሰጠት እንዳለባቸው በፍኖተ ካርታው መካተቱን ዶክተር ተስፋዬ ገልጸዋል። "የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታው ግብዓቶች ተጨምረውበት የሚሻሻል በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የሚሰጡ አስተያያቶቹ ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ" ብለዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ከትናንት ጀምሮ  በአዲሱ የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ትኩረት በማድረግ  ውይይት እያካሄዱ ነው ፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም