አምባሳደሮች የኢትዮጵያና የወከሉትን አገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል

67
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 አምባሳደሮች በስራ ቆይታቸው የኢትዮጵያና የወከሉትን አገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አስገነዘቡ። ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የቬትናም፣ የቤልጂየም፣ የኳታርና የዴንማርክ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዋል። አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ አምባሳደሮቹም ይህንኑ የበለጠ እንዲያጎለብቱ ማሳሰባቸውን የፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል። አምባሳደሮቹ በአገሮቻቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለው በግብርና፣ በጸጥታና ደህንነት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ጠንክረው እንዲሰሩም ጠይቀዋል ብለዋል። ተሿሚዎቹ አምባሳደሮች በበኩላቸው በስራ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሚስ ካሪን ፖለሰን የዴንማርክ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማበረታታት ግኝኑነቱን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል። አምባሳደሯ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ማሻሻያ እርምጃ ዴንማርክ በቅርበት እንድትደግፍ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም አክለዋል። በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሀሚድ ሞሀመድ አል ዶሳሪ ደግሞ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲጎለብት ለመስራት ቃል ገብተዋል። በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ፍራንኮስ ዱሞንት እና የቬትናም አምባሳደር ንጉየን ኪም ዶንህ በበኩላቸው በአገሮቻቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጎልበት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም