በጋምቤላ ከተማ አንጻራዊ መረጋጋት እየታየ መምጣቱን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ

53
ጋምቤላ መስከረም 29 /2011 በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሥራውን ከጀመረ በኋላ በከተማው አንጻራዊ መረጋጋት እየታየ መምጣቱን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ። በከተማው የተፈጠረውን የሰላም ችግር በአጭር ጊዜ ወደ ነበረበት ለመመለስም በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳሬክቶሬት ዳይሬክተርና የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ሙሃመድ ተሰማ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኮማንድ ፖስቱ በጀመራቸው የጸጥታ ሥራዎች ከተማዋ በአንጻራዊነት እየተረጋጋች ነው። ከሁለት ሳምንት በላይ ተዘግተው የነበሩ የንግድ ተቋማት ከትናንት ጀምሮ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። "የመንግስት ተቋማትም የመደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ከተቋማቱ  ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ሥራቸውን እንዲጀምሩ መግባባት ላይ ተደርሷል" ሲሉም አመልክተዋል። ኮማንድ ፖስቱ ከነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን በከተማው በተፈጠረው ችግር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥራ በማዋል ጉዳያቸውን እያጣራ እንደሚገኝም ሜጀር ጀኔራል ሙሃመድ ተናግረዋል። እንደሜጀር ጀኔራል ሙሃመድ ገለጻ ኮማንድ ፖስቱ በከተማው የተረጋጋ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ ህዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ ችግሩ በዘለቂነት የሚፈታበትን ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅቶ ለመተግበር እየሰራ ነው። የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ትልቁ ኃላፊነት የህዝብ መሆኑን የጠቆሙት ጄነራሉ ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ ሰላሙን ወደነበረበት ለመመለስ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በጋምቤላ ከተማ ተዘዋውረን ካናገርናቸው ነጋዴዎች መካከል አቶ ዘራይ ጽጊ በሰጡት አስተያየት በከተማው በተፈጠረው ችግር ለሁለት ሳምንት የንግድ ስራቸውን ቢያቋርጡም ከትናንት ጀምሮ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። በከተማው ተከስቶ የነበረ የሰላም ችግር በጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት በአሁኑ ወቅት እየተረጋጋ መምጣቱንና ንግድ ቤቶችም በአብዛኛው ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ መንገሻ አባኪሮስ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም