በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 250 የቀበሌ ቤቶች ለችግረኞች ተላለፉ

77
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 250 የቀበሌ ቤቶች በከፋ የቤት እጦት ችግር ላይ  ለሚገኙ ነዋሪዎች ተላልፈው ተሰጡ። ቤቶቹ ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ በተካሄደ የተቀናጀ ፍተሻ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በሌሎች አካላት ተይዘው የነበሩና አስተዳደሩ በወሰደው እርምጃ እንዲለቀቁ የተደረጉ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በተገኙበት ስነ-ስርዓት ነው እነዚሁ ቤቶች ለሚገባቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ዛሬ የተሰጡት። በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘው ያሉ ቤቶችን የመለየትና ለችግረኞች የማስተላልፍ ስራ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  ምክትል ከንቲባ ታከለ የቤቶቹን ቁልፍ ለችግረኞቹ ባስረከቡበት ወቅት አስታውቀዋል። አዲስ አበባ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎች የተከናወኑባት ቢሆንም ድሃ ነዋሪዎችን ጨምሮ አሁንም ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች የሚስተዋሉባት ናት። አስተዳደሩ የጠጠር ማምረቻንና ታጥረው የተቀመጡ የፓርክ ቦታዎችን ጨምሮ ወጣቱን ባለስራ ለማድረግ የሚያግዙ እድሎችን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትንም በማከናወን ላይ መሆኑን ኢንጂኒየር ታከለ ገልፀዋል። "ማንም በህዝብ ሃብትና ጉልበት የተሰሩትን የቀበሌና የጋራ መኖሪያ ቤት ከአንድ በላይ መያዝ አይችልም" ያሉት ኢንጂኒየር ታከለ ህብረተሰቡ የተሻለ ከተማ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደግ ጠይቀዋል። የልደታ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው እንደተናገሩት በመኖሪያ ቤቶች ላይ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ አላግባብ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን የመለየት፣ የፈራረሱትንና ታሽገው የተቀመጡትን የማጥራት ተግባር ተከናውኗል። በዚህም መሰረት በተከናወነው ተግባር 250 ቤቶች መለየታቸውን ገልፀዋል። የልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማው ማሙየ ደግሞ ህገ-ወጥ ቤቶቹን ለማስለቀቅ ብዙ ውጣ ውረድ እንደነበረው አስታውሰው በቀጣይም የቀሩትን ህገ-ወጥ ቤቶች ለማስለቀቅ በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በርካታ ሰዎች ከ2004 ዓ.ም በፊት የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሷቸውና የራሳቸውን ቤት ገንብተው ቢኖሩም በወቅቱ ከአመራሩ ጋር በነበራቸው አላስፈላጊ ግንኙነት ላለፉት ስድስት ዓመታት ቤቶቹን አላስረከቡም። ስለሆነም ይህን ህገ ወጥ ተግባር በመተው ቤቶቹን እንዲመልሱ የማግባባት ተግባር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረው ህዝቡም ቤቶቹን ለማስመለስና አሳድሶ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ለመስጠት ለሚደረገው ጥረት በጋራ እንዲሰራ አሳስበዋል። በክፍለ ክተማዋ የሚኖሩት የቤት እድለኛ መንግስት ላደረገላቸው የቤት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በሹፌርነት ይተዳደሩ የነበሩትና በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ለ32 ዓመታት ከሰው ቤት ጥገኛ የሆኑት አቶ ግደይ ደስታ ከእድለኞቹ መካከል ናቸው። የቤት እድለኛ በመሆናቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሌላዋ እድለኛ ወይዘሮ ለይላ ሙሳ በበኩላቸው ከአንድ ልጃቸው ጋር ከሰው ተጠግተው የሚኖሩበት ቤት በክረምት ወቅት ዝናብና ንፋስ የሚያስገባ መሆኑን አስታውሰዋል። አሁን ያገኙት ቤት ግን ካሳለፉት ችግር እንደሚታደጋቸው ነው የገለፁት። በዛሬው እለት የተላለፉት ቤቶች የደሃ ድሃ የሆኑ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በትግል የነበሩ የሰራዊት አባለትና ክራይ ከፍለው መኖር የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው። ክፍለ ከተማው እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ቤቶች ከክፍለ ከተማው ባለ ሃብቶች ጋር በመሆን የእድሳት ተግባር ማከናወኑም ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም