ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን----የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አባላት

73
ዲላ መስከረም 29/2011 በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌ.ህ.ዴ.ድ) አመራሮች ገለፁ ፡፡ በውጭና በሀገር ውስጥ የነበሩ የድርጅቱ አመራሮች ትላንት ዲላ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አለሳ መንገሻ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በነበረው መከፋፈልና የጠበበ የፖለቲካ ሥነ-ምህዳር አባላቱ ከአካባቢያቸው ርቀው ተሰደው ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና አጋሮቻቸው እያራመዱት ባለው አስተሳሰብ አንዲት ኢትዮጵን የመገንባት ራዕይ መፈጠሩን ተናግረዋል። የድርጅቱ አመራሮች ሀገራዊ አንድነቱን በመደገፍ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል። "በኢህዴግ ውስጥ ካሉ የለውጥ አራማጆች ጎን በመቆም  በሀገር ግንባታ ውስጥ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን" ብለዋል ፡፡ " በዞኑና አካባቢው ያሉ ህዝቦች በሰላምና በአንድነት እንደኖሩና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን " ሲሉም ተናግረዋል ። ሌላው የድርጅቱ አመራር አቶ ተፈራ ጅግሶ በበኩላቸው በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዜጎች ለሞት፣ ለእንግልትና ለመፈናቀል መዳረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ "ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁላችንም የለውጡ አንድ አካል በመሆን በጋራ ጥረት ማድረግ ይገባናል" ብለዋል ፡፡ የዞኑ ህዝቦች በዓለም ገበያ ተመራጭ የሆነ ቡና እያመረተ በድህነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመቀየር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም አስረድተዋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተደዳሪ አቶ ኃይለማርም ተስፋዬ "ባለፉት አመታት እርስ በእርሳችን ስንጠላለፍ መቆየታችን በርካታ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ፡፡ "ህዝብን ለማገልገል የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት መሆን ግድ አይልም" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በማንነት ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በያለበት ዘርፍ አገሩንና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  ሊሠራ እንደሚገባ አስታውቀዋል ። በአቀባበል ስነ ስርአቱ ላይ  የጌዴኦ ዞንና የዲላ ከተማ አመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል ፡፡ የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌ.ህ.ዴ.ድ) ከተመሰረተ 27 ዓመት እንደሆነው ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም