የተፈቀደልን የደሞዝ ማሻሻያ ተግባራዊ ባለመሆኑ የኑሮ ጫና ፈጥሮብናል-በሐረር ደንብ አስከባሪዎች

109
ሀረር መስከረም 29/2011 የተፈቀደልን የደሞዝ ማሻሻያ ተግባራዊ ባለመሆኑ በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል ሲሉ የሀረሪ ክልል ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ገለፁ፡፡ የክልሉ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት በበኩሉ  የደሞዝ ማሻሻያው የአሰራር ክፍተት ያለበት በመሆኑ ማስተካከያ ሲደረግ መቆየቱን ገልጿል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ማርታ ካሳሁን እንዳሉት ”ከሶስት አመት በፊት በ1ሺህ 400 ብር ደሞዝ በተቋሙ  ተቀጥረዋል ። "በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም  ጀምሮ የደሞዝ ማሻሻያ እንዳደረገ በደብዳቤ ቢያሳውቀንም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልተደረገም'' ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሚከፈላቸው ደሞዝ  ኑሯቸውን በአግባቡ ለመምራት አዳጋች ከመሆኑም በላይ የስራ ተነሳሽነታቸውን እንዲቀንስ ያደረገ መሆኑን ተናግራል ። ''የተደረግልን የደሞዝ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላትን ብንጠይቅም ምሳሽ አላገኘንም'' ያሉት ደግሞ የተቋሙ ሰራተኛ አቶ ኻሊድ ሁሴን ናቸው፡፡ በተቋሙ 10 አመት ማገልገላቸውን የገለፁት አቶ ኻሊድ የሚከፈላቸው ደሞዝ አራት ልጆቿቸውን ለማስተማር አዳጋች እየሆነባቸው መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ "እየሰራን ያለነው ኃላፊነት የሚጠይቅ ስራ ነው" ያሉት አቶ ከበደ ማርቆስ የደሞዝ ማሻሻያውም ሆነ ውዝፍ ክፍያ እስካሁን እንዳልደረሳቸው ገልፀዋል ። መንግስት የህዝቡት ቅሬታ ደረጃ በደረጃ እየፈታ ባለበት በአሁኑ ወቅት በክልሉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አስረድተዋል። የክልሉ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የደሞዝ ማሻሻያው የዲፕሎማና የዲግሪን ትምህርት ደረጃን ማእከል ያደረገና የተቋሙን ሰራተኛ ተጠቃሚ የማያደርግ በመሆኑ የአሰራር ክፍተት እንደነበር እስታውሰዋል ። ጽሀፈት ቤቱ በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርን ተሞክሮ በመውሰድ አዲስ የደሞዝ ማስተካከያ ተሰርቶ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ በመሆኑ በቀጣዮቹ ወራቶች ተግባራዊ እንደሚሆን ሀላፊው አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም