ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ሊከፍት ነው

67
ሐረር መስከረም 29/2011 ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ሦስት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን እንደሚከፍት አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ይልፋሽዋ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በጆግራፊና አካባቢ ጥናት በዶክትሬት ዲግሪ እንዲሁም በኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግና በኮሙኒኬሽን ሲስተም ኢንጂነሪንግ በሁለተኛ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል። የትምህርት መርሀ ግብሮቹ በስነ ምህዳር፣ ስነ ህዝብና አየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት፣ ስርጭትና ማስፋፋትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዶክተር ይልፈሸዋ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀግብሮች  ከ26 ወደ 27 እንዲሁም 125 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 127 ከፍ ያደርገዋል። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በበኩላቸው ተቋሙ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 4 ሺህ 621 አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የተማሪዎች መኝታ፣ መማሪያ፣ ቤተ መጻህፍትና መመገቢያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ አዳዲስ ተማሪውም ወደ ተቋሙ ሲመጡ እንዳይስተጓጎሉም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ የሚቀበላቸውን አዳዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ 27 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በርቀት፣ በተከታታይና በክረምት የትምህርት መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ያሰለጥናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም