“ዓይንና ጆሮ… ለላይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት”

151
በእንግዳው  ከፍያለው  ከባህር ዳር ኢዜአ “ዓይኔ ዓለም አዬ እገሬ ደርሶ… አይኔ አለም አየ እግሬ፤ የድንጋይ ውጋግራ የድንጋይ ምሰሶ” እያለ በየዓመቱ ከታህሳስ 19-29 ከአራቱም ማዕዘን ወደ አካባቢው የሚተመው ምዕመን የሚዘመርለት፣ የቤዛ ኩሉ… ዓለም… ዝማሜ በማሜ ጋራው የሚደምቅበት፣ ካህናቱ በድርብ ጥንግ፣ በካባ፣ በሸማ… አምረውና ተውበው ነፋስ እንደሚያወዛውዘው ሸምበቆ የሚዘምቡት … እና ሌሎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚርቡበት ቦታ ነው። ዓለም እጹብ ድንቅ… እያለ የሚመስክረለት ቅርስ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት -  አዎን ! የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እፁብ ድንቅ ነው ። ከአውሮፓ ፖርቹጋል አገር ተነስቶ ወደ አፍሪካ አህጉር የመጣው ቄስ ፍራብንሲስኮ አልቫሬዝ እኤአ በ1520 ወደ ኢትዮጵያ ደርሶ በተለያዩ አካባቢዎች እየዞረ ሲጎበኝ ላሊበላ ይደርሳል። የላሊበላ ቅርሶችን በአንክሮ ከተመመለከተ በኋላ እጹብና አስደናቂ ስለመሆናቸው ሲጽፍ “ስለነዚህ አብያተ ክርስትያናት ብዙ ብጽፍ ማን ያምነኛል፤ ነገር ግን በእግዚአብሄር ፊት ቃል እገባለሁ ። የጻፍኩት ሁሉ እውነት ነው” ሲል መስክሯል ። አብያተ ክርስትያናቱም ቤተ መድሃኔ ዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ አማኑኤል፣  ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ ጎልጎታ፣ ቤተ ደብረ ሲና፣ ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ መርቆርዮስና ቤተ አባሊባኖስ የመሳሰሉትን ይገኙበታል ። በዓለም ደረጃ የሚታወቁት እነዚህ አብያተ ክርስትያናት በ12ኛው ክፍለ ዘመን የዛጉዌ ንጉሰ ነገስት በነበረው አጼ ላሊበላ የተገነቡ መሆናቸው ይታወቃል። የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እጹብና ድንቅ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው የታነጹት ወጥ ከሆነ አንድ አለት የተፈለፈሉ በመሆናቸው ነው። አፈላፈላቸወም ወጥ ሆነው ራሳቸውን ችለው የቆሙና በከፊል ከዋናው አለት ጋር አናታቸው ተያይዞ የተገነቡ ይገኙበታል። የአንዱ አሰራር ከሌላው ጋር የሚለያዩባቸው የዲዛይን፣ የቅርጽ፣ የአሰራርና ትርጓሜ አላቸው። ለዓለም አስደማሚ የሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ እና ዋናው ከላይ ወደታች የተፈለፈሉ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል ። አለትን ከላይ ወደ ታቸ መፈልፈል እንኳን በኋላ ቀር መሳሪያ እና በሰው ጉልበት ቀርቶ አሁን ላይ ዘመኑ ባመጣው እስካቬተር እንኳ አፈር ይዛቅ እንደሆነ እንጂ ዓለቱን መፈልፈል ከቶ አይቻለውም። ዓለቱን ለማውጣት አካፋው ተነቅሎ መሰርሰሪያ መሳሪያ /ጃማከር/ መግጠም ይጠይቃል። ከ900 ዓመታት በላይ እድሜ ጠገብ የሆኑት ቅርሶች አሁን ላይም ከኪነ ጥበብ ውበታቸውና ግርማ ሞገሳቸው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ላሊበላ ከተማ ላይ ይገኛሉ። አሸተን ማርያም፣ ነዓኩቶለዓብ፣ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ አርባእቱ እንስሳ፣ ገነተ ማርያም፣ መኪና መድሃኔ ዓለም፣ ሳርዝና ሚካኤልና ሌሎች ከአለት የተፈለፈሉና በዋሻ ውስጥ የተገነቡ አብያተ ክርስትያናት በዙሪያውና በቅርብ ርቀት የሚገኝበት አካባቢ ነው። አካባቢውን ለሚያጠናና ለሚመረምር ሰው “የቱሪዝም ሜትሮፖለቲታንት” ሊያሰኘው የሚችል ሃብትና ጸጋ ተጎናጽፎ የሚገኝ አካባቢ መሆኑ ግልጽ ነው። የዓለምን ህዝብ ቀልብና ልቦና የሳቡትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በ1970 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። መመዝገባቸውም ከተለያዩ የዓለም አገራት ጎብኝዎች ወደ አገራችን እንዲመጡ አስችሏል። ላሊበላን ለማየት ብለው የሚመጡ ቱሪስቶችም ከአስጎብኝ ድርጅቶች፣  ሌሎች አካላት በሚያገኙት መረጃ መሰረት እንደ አክሱም፣ ጎንደር፣ የጀጎል ግንብና ሌሎች ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሃብቶችን ለምሳሌ ፓርኮችን፣ የዱር እንስሳትን፣ ፏፏቴዎችን፣ ሃይቆችንና ሌሎች የመስህብ ሃብቶችን በመጎብኘት ወደ አገሩ ሲመለስ ስለ አገራችን እንዲሰብክ በር ከፍቷል። የላሊበላ አብያተ ክርስትናያት ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ደረቱን ገልብጦ ከሰጠ አለት ነው የተፈለፈሉት። በመሆኑም ከሰዓት በኋላ በተለይም ፀሃይ ወደ ምዕራብ እያጋደለች ስትመጣ የፀሃዩ ሃይል ሙሉ በሙሉ ህንጻዎቹ ላይ ያርፍባቸዋል። የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስባቸው በጥሩ ዲዛይን ተፋሰስ በራሱ በላሊበላ የተሰራላቸው ናቸው። ህንጻዎቹ የቀን ጸሃዩ፣ የሌሊት ቁሩ፣ የክረምት ዝናቡ፣ የማታ ነፋሱ… እየተፈራረቀባቸው ይህን ያህል እረጅም ዘመን መቆየት ችለዋል። በእድሜ ብዛት፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በአብያተ ክርስትያናቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በአራት አብያተ ክርስትያናት ላይ የተገነባው መጠለያ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል። ሲገነባ ግን ለአምስት ዓመታት ብቻ ያገለግላል ተብሎ እንደነበር የቅዱስ ላሊበላ አድባራት አስተዳዳሪ የሆኑት መምህር አባ ጽጌ ስላሴ ገልጸዋል። የተገነባው ጊዜያዊ መጠለያ ይቆያል ከተባለው ጊዜ በተጨማሪ አምስት ዓመት በመቆየቱ ምክንያት በህንጻዎቹ ላይ ጉዳት ማድረሱን እየተነገረ ነው ። ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ አሁን ላይ ጉዳቱ በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ፣ በእዝነ ልቦና የሚስተዋል  በመስተዋሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል። መጠለያውን የሚሸከሙት በእያንዳንዳንዱ አብያተ ክርስትያናት በአራቱም ማዕዘናት ከብረት የተሰሩ ከባድ ምሰሶች አሉት። በእያንዳንዱ ማዕዘን ደግሞ እስከ አራት የሚደርሱ ክብደታቸውን በውል ለማወቅ የሚያስቸግር ብረቶች ቆመዋል። ልብ በሉ በአንዱ ቤተ ክርስትያን ብቻ 16 ምሰሶዎች አሉ ማለት ነው። የእያንዳንዳንዱ ክብደት ደግሞ አሁን በከተሞች እየተተከለ ካለው የመብራት ኮንክሪት ፖል ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይመስልም። እነዚህ ምሰሶዎች በቤተክርስቲያኑ አናት ላይ በብሎን እየተጋጠጠመ ተጠላልፎ የሚገኘውን በርካታ አግዳሚ ብረቶች የሚሸከሙ ናቸው። የእነዚህ አግዳሚ ብረቶችም ተጠላልፈው ከማየት ውጭ ቁጥራቸውንና ክብደታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል። በሸራ ተወጥሮ በላይም በታችም የተሸፈነው ብረት ብዛት ከታች ሆነው ሲመለከቱት እንደ ሸረሪት ድር ተጠላልፎ ይታያል።   አሁን ላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ እንዲጮህ፣ እንዲያለቅስ፣ ፣ እንዲተክዝ ያደረገው በአራቱም ተሸካሚ ምሰሶዎቹ ከክብደታቸው የተነሳ የቆሙበት አለት እየተሰባበረ ሲመጣ በመታየቱ ነው ።ምሰሶዎቹ ከነበሩበት እየተንሸራተቱ፣ እየሸሹና ቦታቸውን እየለቀቁ መምጣታቸው በግልፅ ጉዳዩ አስደንጋጭ አድርጎታል ። ምሰሶዎቹ እየተንሸራተቱ ሲመጡም የመውደቅ እድላቸው ሰፊ ነው። ምሰሶዎቹ ባይወድቁ እንኳ ከላይ የተገጣጠሙት አግዳሚ ብረቶች ብሎናቸው እየላላ ወይም እየተሰባበረ መምጣቱ የማይቀር ሃቅ ነው። አንዱ ብረት ከወደቀ ደግሞ ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራውን ቤተ ክርስትያን እንዳልነበር እንደሚያደርገው ነው ነዋሪዎቹ የሚገልጹት። ምሁራንም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በጥናታቸው አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ምሁራን በተከታታይ ዓውደ ጥናቶችና ሲምፖዚየሞች እንዳቀረቡት ከሆነ ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያየዞ እየተከሰተ ባለው ተለዋዋጭ ሁኔታ መጠለያው ሲሰራ የነበረው የነፋስ ፍጥነት አሁን ላይ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በእጥፍ የሚለውን ቃል አስቡት 10 ከነበር 20፤ 50 ከነበር 100… ማለት ነው። ይህም የችግሩን አሳሳቢነት በተጨባጭ ማስረጃ ያረገገጠ ነው። ስለዚህ ቅርሶቹ የህዝብና የአገር ሃብት በመሆናቸው መንግስትና የሚለከታቸው አካላት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ያሉት የአካባቢው ነዋሪና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር የሁለተኛ ዓመት የ2ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ይሄነው መልኩ ናቸው። የችግሩ አሳሳቢነት ሲገልፁት የእያንዳንዳንዱን ብረት ውፍረትና ክብደት ላዬ እንኳን እንቅልፍ ሊያስተኛ ቀርቶ እህል ውሃ የሚያስቀምስም አይደለም በማለት ነው ። ለዚህም ነው በመስከረም 27/2011 ዓ.ም የላሊበላ ከተማና የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት በሰላማዊ ሰልፍ ቅርሱ እየደረሰበት ያለውን ችግር ለአገራችንና ለዓለም ህብረተሰብ እንዲሁም ለመንግስት ማስገንዘብ የተፈለገው። ባለፉት ዓመታት በህዝቡ ጩኸት የተነሳ በርካታ ጥናቶች ተጠንተዋል ። ጥናቱን አስመልክቶ ዓውደ ጥናቶችና ሲምፖዚየሞች ተካሂደዋል። መጠለያውን ለማንሳትና ለመጠገን 300 ሚሊየን ብር ወጭ እንደሚጠይቅ ተረጋግጧል። ዋናው ችግር አሁን ካለው የወቅቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የአገራችን መሪዎች በየጊዜው መቀያየራቸው ነው። የሰሙት ወንበሩን ሲለቁ ያልሰሙት ሲመጡ ለእነሱ የችግሩን አሳሳቢነት እንደገና ሃብሎ ማስረዳት ደግሞ በቅርሱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በአጭር ጊዜ ከማስወገድ ይልቅ በጊዜ ብዛት የሚፈራው ውድመት እንዲከሰት ጊዜ መስጠት ነው። የቀድሞዋ የቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት እቦታው ድረስ ሄደው አይተው እንደመንግስት መውሰድ የሚገባንን የጋራ መፍትሄ እንወስዳለን ብለው ነበር። መንግስትም ጉዳዩን ተገንዝቦ ምላሽ እንደሚሰጥ በወቅቱ በሚዲያ ተነግሯል። መሪዎች ሲቀያየሩ የተገባው ቃል ሁሉ የውሃ ሽታ በመሆኑ የደነገጠው የላሊበላና አካበቢው ማህረሰብ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ተገዷል። ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶም አይንና ጆሮውን የሚሰጠው አንዳች ሃይል እየተመኘ ነው። አሁን ላይ የላሊበላና የአካባቢው ማህበረሰብ “አዲስ ታሪክ መስራት ባንችል እንኳን ያለንን ታሪክ እንጠብቅ” በሚል መሪ ቃል ያካሄደው ትዕይንተ ህዝብ አዲሱ የዶክተር አቢይ አህመድ መንግስትም በላሊበላ ቅርሶች ላይ የተጋረጠውን አደጋ በውል በመገንዘብ ለመፍትሄው ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ የሚያስገነዝብ ነው። ዓለም ኢትዮጵያን ሲያስብ ላሊበላን፤ ላሊበላን ሲያስብ ኢትዮጵያን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ቅርሱን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ አገራት ቱሪስቶች በቆይታቸው የሚያፈሱት ዶላርም የመንግስትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመቅረፍ ለዘመናት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የአገራችን ህዝቦችን ሊያውቁት ይገባል። ይህን ጉዳይ በመገንዘብ የላሊበላ ቅርስ የክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን የኛም ነው ። እኛንንም ያሳስበናል ብለው ከክርስቲያኖች ጋር ሙስሊም የአካበቢው ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ቅርሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ለመሆኑ ማሳያ ነው። እስላም ክርስቲያን፤ አማራ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ… በጋራ ሊቆሙለት፣ በጋራ ድምጻቸውን ሊያሰሙለት፣ በጋራ መፍትሄ የሚያፈላልጉለት የጋራ ቅርስ፣ የጋራ እሴት፣ የጋራ የአገር ሃብት ነው። በጋራ ሲጠቅመን የኖረና ለወደፊትም በጋራ የምንጠቀምበት ቅርስም ነው። በጋራ በመቆምም አይንና ጆሮ… ልንሰጠው የሚገባ ቅርስ ነው። የተጠየቀው 300 ሚሊየን ብር በአገር ደረጃ ሲታሰብ ያን ያህል ከባድ ሆኖ ሳይሆን ጉዳዩን በባለቤትነት ይዞ የሚሰራ በመጥፋቱ የተከሰተ ነው። መጠለያውን ያስገነባው ዩኔስኮ፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማት ላሊበላን ለማዳን እጃቸው አጥሮ አይመስለኝም። ያም ቢቀር ከ85 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የጠየቀውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመተባበር እየገነባ ያለ ህዝብ የላሊበላን ቅርሶች ለማዳን ያቅተዋል የሚል አስተሳሰብም ሆነ አመክንዮ የሚኖር አይመስልም። ዓለም በፈጠራ በተሞላችበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እኛ አባቶቻችን አንጸው ያስረከቡንን ቅርስ በእንዝህላልነት እስኪወድም መጠበቅ ከሞኝነትም በላይ ሆኖ ነው የሚታየው። ለአምስት ዓመት ተብሎ የተገነባው መጠለያ ገና አምስተኛ ዓመቱ ላይ ነበር የሚመለከተው አካል ቀድሞ ርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ የነበረበት። በተለይም የባሀልና ቱሪዝም እንዲሁም የቅርስና ጥበቃ መስሪያቤቶች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በመሆኑ ይህን ያህል ጊዜ ወስዶ ህዝብ አደባባይ እስኪወጣ ድረስ መጠበቅ አልነበረበትም። ያው አንዱ የተቋማዊ አሰራር ደካማነታችን ማሳያ ነው የሆነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም