በአካባቢያችን ትምህርት ቤቶች በመገንባታቸው ያቋረጥነውን ትምህርት ለመቀጠል ችለናል....ነዋሪዎች

56
ባህር ዳር መስከረም 29/2011 በአካባቢያቸው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው በአቅም ችግር ምክንያት ያቋረጡትን ትምህርት ዳግም ለመቀጠል እንዳስቻላቸው ተማሪዎች ተናገሩ። በክልሉ ከ195 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውም ተመልክቷል። በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሁለቱ ይጎማ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ሲሳይነህ ውበት ለኢዜአ እንደገለጸው ወላጅ አባቱን በህይወት ማጣቱን ተከትሎ በአቅም ማነስ ምክንያት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ለአራት ዓመት ማቋረጡን ገልጿል። የግብርና ስራውን በኃላፊነት በመስራትና ሁለት ታናናሽ እህቶቹ ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ በባህር ዳር ከተማ ቤት ተከራይቶ በመደገፍ ወደዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ማድረጉን ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የገንጂ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ዘንድሮ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩ በአቅም ማነስና በርቀት ምክንያት ለአራት ዓመታት ያቋረጠውን ትምህርት ዳግም ለመቀጠል እንዳስቻለው ተናግሯል። ተማሪ ስንታየሁ ወርቁ በበኩሏ ወደዘጠነኛ ክፍል የተዛወረችው በ2009 ዓ.ም ቢሆንም በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩና ሌላ ቦታ ቤት ተከራይታ መማር ባለመቻሏ ትምህርቷን ለአንድ ዓመት አቋርጣ መቆየቷን ገልጻለች። በአሁኑ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአካባቢያቸው ማስተማር በመጀመሩ ያቋረጠችውን ትምህርት ርቃ ሳትሄድ ለመማር ዕድል ማግኘቷንና በእዚህም ደስተኛ መሆኗን ነው የተናገረችው። የደብረ መዊ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራ በመጀመሩ ለዘጠኝ ዓመት ያቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር እንዳስቻለው የተናገረው ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ የደብረመዊ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ አብርሃም ካሳ ነው። "በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ትምህርት ቤት ዘንድሮ በመከፈቱ ደጋፊ በማጣት ለዓመታት ያቋረጥኩትን ትምህርት ካቆምኩበት ለመቀጠል ችያለሁ፤ በእዚህም ዳግም የተወለድኩ ነው የመሰለኝ።" ብሏል። በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሁለቱ ይጎማ ቀበሌ ነዋሪና የትምህርት ቤቱ የወላጅ መምህር ህብረት ሰብሳቢ አርሶ አደር አማረ ያዜ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ መገንባት ወላጆችንና ተማሪዎችን ከወጭና እንግልት ማዳኑን ተናግረዋል። "ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ለአራት ልጆቼ በባህር ዳር ከተማ ቤት ተከራይቼ ለእያንዳንዳቸው በወር እስከ 1 ሺህ ብር ወጭ እያደረኩ በማስተማርና ወደ ዩኒቨርሲቲ በማስገባት ለማስመረቅ ችያለሁ" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በቀበሌያቸው የተገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ዘንድሮ ወደዘጠነኛ ክፍል ያለፈው ልጃቸው ከአጠገባቸው ሳይርቅ የመማር ዕድል እንዲያገኝ ማድረጉንም ተናግረዋል። የአካባቢው ህብረተሰብም ለውስጥ ቁሳቁስ ማሟያ የሚሆን ከ120 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት ለትምህርት ቤቱ አስተዋፅኦ ማድረጉን አርሶ አደር አማረ አስረድተዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈራ ፈይሳ በበኩላቸው በ195 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ 24 ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶቹ እያንዳንዳቸው ስምንት የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ የአስተዳደር፣ የቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጻህፍትና የአይሲት ክፍሎችና የያዙ መሆኑንም አስታውቀዋል። ትምህርት ቤቶቹ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን በአካባቢው ከ9 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ማስቸላቸውን ገልጸው በተለይ ታዳጊ ተማሪዎች በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። የክልሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 44 በመቶ ወደ 54 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘውን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም