ሰመራ ከበረሃነት ወጥታ ወደ ውብ ከተማነት እየተለወጠችና በእድገት ጎዳና የምትገኝ ከተማ ናት

64
አዲስ አበባ  ግንቦት 12/2010  ከሃያ ዓመት በፊት አካባቢው በጦር ሰፈርነት ይታወቅ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች “ትናንት በረሃ ነበር” እያሉ ይገልጹታል። ያ በረሃ በሂደት ወደ አነስተኛ መንደርነት ተለወጠ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የከተማ ገጽታ ይዞ እየተገነባ ዕለት ከዕለትም እያደገ መምጣቱን ይመሰክራሉ፤ ነዋሪዎቹ። የአካባቢው ነዋሪዎች ‘ከዚያ በረሃ ይህች ውብ ከተማ እንዴት ተወለደች ብለን ስናስብ እንደ ህልም የምናስታውሳቸው ብዙ እውነቶች አሉ’ የሚል ሀሳብ ያንጸባርቃሉ። የአፋር ብሄራዊ ክልል ርእሰ ከተማ ሰመራን እድሜ ቆጥረውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘውን ውጤት በማጤን ገና ብዙ ይሰራል ሲሉም ተስፋ ያደርጋሉ። ሰመራ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ነው የአፋር ክልል መዲና በመሆን  የተመረጠችው። በህዝቡ ፍላጎት  የከተማ ፕላን ወጥቶላት በአዲስ መልክ የተቆረቆረችው ሰመራ ዛሬ ላይ ከዘመናዊ ከተሞች ተርታ የምትሰለፍ ሆናለች። በ1996 ዓ.ም አንዳንድ የመንግስት ተቋማት በስፍራው መከፈት ሲጀምሩ ሌሎች መሰረተ ልማቶችም በተከታታይ ዓመታት ወደ ግንባታ መግባት መጀመራቸው ነው የሚነገረው። ይህ ከመሆኑ በፊት የነበረውን ሁኔታ ግን ነዋሪዎቹና የከተማው አመራሮች እንዲህ ያስታውሱታል።  “ሰመራ በመጀመሪያ የተወሰነ መንደር የሚባል ከተማ ነበረበት ደርግ ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ወደ ሎጊያ ከተማ ቀላቀላት ከዚያ በኋላ የጦር ካምፕ ሆና ነበር˝ በማለት የተናገሩት አቶ ነስሪ ቡራሃባ  ናቸው። ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ˝መግቢያ ምንም የለም ትምህርት ቤትም የለም የህክምና አውታሮችም ጤና ጣቢያዎችም ሁሉም ነገር የለም ያው እናቶችም በወሊድ ምክንያት ስንት የሚሞቱ እናቶች በውሃ እጦት ምክንያት ብዙ ህዝብ እያለቀ ነበር˝ በማለት ትዝታዋን አንስታለች፡፡ ለአፋር ክልል ከተሞችና መንደሮች አማካይ ቦታ ላይ ትገኛለች ተብሎ የተመረጠችውና በፕላን የተገነባችው ሰመራ በአሁኑ ወቅት 97 ጤና ጣቢያዎች አሏት። ጤና ኬላዎቿም ከሀያ የማይበልጡ ነበሩ፤ አሁን 404 ደርሰዋል፡፡ የሰመራ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሳ ማህሙዳ ከመዋለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርት ተቋማትም በከተማዋ እየተበራከቱ መጥተዋል ይላሉ፡፡ በክልሉና በሰመራ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች ለክልሉ ልማት በሚበጀተው ገንዘብ ላይ ግልፅ ውይይት የሚያደርጉበት፣ የሚፈልጉትን ልማት የሚመርጡበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርአትም እየተገነባ መሆኑን ነው የሚናገሩት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሳ ማህሙዳ። ይህ የሆነው ከግንቦት 20 የህዝብ ድል በኋላ የስርዓት ለውጥ በመምጣቱ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የአፋር ህዝብ የራሱ የሆነ የአስተዳደር ስርዓትና የራሱን መገለጫ ከማዋቀር ባለፈ ሰመራ እንድትመሰረትና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በአማካይ ቦታ እንዲያገኝ ማድረጉን ይናገራሉ። ሰመራን የወለዳት “ነፃነታችን ነው” የሚሉት አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች፤ በተለይም ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች እኩል መታየታቸውን ነው በዋናነት የሚያነሱት። ዛሬ በከተማዋ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና እድገት ይታያል፤ ይህም በተለይ ለአፋር ክልል ነዋሪዎች የተለያዩ የስራ ዘርፎችንና የእድገት በሮችን ከፍቷል ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ። ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ በሎጊያና ሰመራ ከተሞች ለ24 ዓመታት በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከአፋር ህዝብ ጋር ሲሰሩ የቆዩና በአሁኑ ሰአት ባለ ሶስት ሆቴል ባለቤት ናቸው። ህገ መንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነትና አብሮ የመስራት፣ ከክልል ክልል መዘዋወርና ሃብት የማፍራት መብት ባያመጣ ኖሮ በአገሪቷ ላይ አሁን የሚታዩ ለውጦች ሊመጡ አይችሉም ነበር ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም