የግብር አሰባሰብ ችግርን ለመፍታት በዘርፉ እየተደረጉ ያሉ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር እየተቀየሩ አይደለም

131
አዲስ አበባ  መስከረም 28/2011 በኢትዮጵያ ያለውን የግብር አሰባሰብ ችግር ለመፍታት በዘርፉ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶችና ምርምሮች ወደ ተግባር የሚለወጡበትን አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ታክስ ጥናት ኔትወርክ አመታዊ የምክክር መድረክ አባላቱና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚህ ወቅት  የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ከግብር ጋር የተያያዘና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮችን ይፈታሉ ተብለው የተጠኑ ጥናቶች ወደ ተግባር ሲቀየሩ አይስተዋልም። የግብር አሰባሰብ ችግሮች አገሪቱን ዋጋ እያስከፈሏት ሲሆን ይህንን ለመፍታትም እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ፍሬያማ ሲሆኑ አይስተዋልም። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአገሪቱ የግብር አሰባሳብ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች የመጨረሻውን ደረጃ እንድትይዝ ያደረጋት መሆኑንም ጠቁመዋል። የታክስ አሰባሰብ ችግሮች ናቸው ተብለው ከተለዩት ውስጥ ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ አነስተኛ መሆን፣ የግብር አስተዳደሩ አቅም ማነስ፣ የግብር ፖሊሲ ችግሮች ዋነኞቹ መሆናቸውን አስረድተዋል። ችግሩን ለመፍታት በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚሰሩ ጥናቶች ወደ ተግባር መቀየርና ፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት የሚጠቀሙበትን አሰራር መዘርጋትና ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል። የታክስ ጥናት ኔትወርክ ዋና ጸሃፊ አቶ ግርማ ገብረጻዲቅ እንዳሉት፤ ኔትወርኩ ከተቋቋመ አንድ ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን በታክሰ  አሰባሰብ ችግሮች ላይ ስድስት ያህል ጥናቶችን አካሂዷል። የዕለት ገቢ ግምት ችግሮች፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ የግብር ከፋዮች አመለካከት፣ ተደራራቢ ግብር ማስቀረትና የግብር ከፋዮች ስልጠና ላይ ነው ጥናቶቹ የተደረጉት። ጥናቶቹ እንዴት ወደ ተግባር ይቀየራሉ፣ ለፖሊስ ግብዓትነትስ እንዴት ይውላሉ በሚለው ላይ ዛሬ ምክክር ተደርጓል። እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፤ ኔትወርኩ ወጣት ተመራማሪዎች በታክስ መስክ ምርምር እያደረጉ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች እጥፍ ዕድገት ብታስመዘግብም ከግብር የምታገኘው ገቢ ግን ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም የአገሪቱ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ችግር እንዳለበት አመላካች ነው። በአሁኑ ወቅት ይህንን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምሮችን በሰፊው ለመጠቀም የአገሮችን ተሞክሮ ለመቀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩም የኡጋንዳና የብሩንዲ ተሞክሮ ቀርቦ የታክስ አሰባሰብ ስርዓታቸውን ለማዘመን የተጠቀሙት ጥናትና ምርምር ስራ ወደ ተግባር መቀየራቸው ከፍተኛ ውጤት እንዳስገኘላቸው ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግብር ከፋዩ መሰብሰብ ከሚገባው ግብር ውስጥ 50 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም