በባሌ ዞን የስንዴ ዋግ በሽታ ለመቆጣጠር የመድኃኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

119
ጎባ መስከረም 28/2011 በባሌ ዞን በአምስት ወረዳዎች የተከሰተውን የስንዴ ዋግ በሽታ ለመቆጣጠር የመድኃኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው አርሶ አደሮች ገለፁ። የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ አምስት ወረዳዎች በስንዴ ቡቃያ ላይ የተከሰተውን የዋግ በሽታ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግሯል። በሲናና ወረዳ ሀሚዳ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ሀጂ ሁሴን አህመድ እንዳሉት በአንድ ሄክታር መሬት ባለሙት የስንዴ ቡቃያ ላይ የዋግ በሽታ ተከሰቷል። የፀረ ዋግ መድኃኒት በአካባቢ ገበያም ሆነ በየደረጃው ባሉት የመንግስት መዋቅሮች ማግኘት ባለመቻላቸው ቡቃያው ለከፋ ጉዳት ሊጋለጥ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል ። አርሶ አደሩ እንዳሉት የሰብል ምርታማነትን የሚቀንሰው የዋግ በሽታ የበለጠ ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር እንዲቻል መንግስት መድኃኒቱን በማቅረብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። ሌላው የጎባ ወረዳ አርሶ አደር አህመድ ሁሴን በበኩላቸው “በሽታው መከሰቱን ባደረኩት ክትትል ቀደም ብዬ ባውቅም በገበያ ላይ ያገኘሁት የፀረ ዋግ መድኃኒት በቂ ባለመሆኑ ማሳውን ሙሉ በሙሉ ከበሽታው መከላከል አልቻልኩም ሲሉ የችግሩን ስፋት ገልጸዋል። የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዳውድ አብዱሪ በበኩላቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት የዋግ በሽታው የተከሰተው በዞኑ ሲናና፣ አጋርፋ፣ ጎባ፣ ጎሎልቻና ጋሰራ በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በባለሙያ በተደረገው ዳሳሳ በአምስቱ ወረዳዎች በስንዴ ምርት ከለማው 79 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 20 ሺህ በሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ በሽታው ተከስቷል ። በአርሶ አደሩ ተሳትፎ በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት እስካሁን ድረስ በ6 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ 3 ሺህ 200 ሊትር ናቱራ፣ ቲልትና ናቲቮ የተባሉ ኬሚካሎች ተረጭተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ በሽታው የተከሰተው በአካባቢው ያለው የአየር ንብረት አመቺ መሆኑና አርሶ አደሮችም በአንድ ማሳ ላይ ተመሳሳይ ሰብሎችን ሳያፈራርቁ  በተደጋጋሚ መዝራታቸው ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ያነሱት የፀረ ዋግ ኬሚካል እጥረት ትክክል መሆኑን ያመኑት  ኃላፊው እጥረቱ ሊከሰት የቻለው ከዚህ በፊት በግል ባለሀብቶች ይቀርብ የነበረው መድኃኒት ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በበቂ መጠን ባለመቅረቡ መሆኑን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በመንግስት ብቻ እየቀረበ ያለው መድኃኒት ከአርሶ አደሩ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አለመሆኑም የራሱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ከኦሮሚያ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮና ከመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አማራጮችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ዳውድ የገለጹት። በዞኑ በ2010/2011 የመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ካለው 389 ሺህ ሄክታር መሬት  ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም