በትግራይ ክልል የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መስህብ ሃብቶችን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው

220
መቀሌ ግንቦት12/2010 በትግራይ ክልል የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መስህብ ሃብቶችን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ የቱሪዝም መስህብ ሃብቶችን በበለጠ አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሂደት ዙሪያ ትናንት በመቀሌ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል፡፡ በክልሉ ተወላጅ የዘርፉ ምሁራን ተነሳሽነት የተቋቋመው ‘‘የክልሉ የቱሪዝም ልማት ኮሚቴ’’ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያግዝ የጥናትና ምርምር ስራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ ተመራማሪና የኮሚቴው አስተባባሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በበቂ አለመኖርና ስለ ቱሪስት መስህብ ሃብቶች በቂ መረጃ አለመኖር ክልሉ ከሃብቱ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ ይህንኑ ችግር ለመፍታት በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ መስህቦችን በሚገባ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያግዙና በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ስድስት መጻህፍት ታትመው ለተጠቃሚዎች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም እምቅ የቱሪዝም ሃብቶቹ ያሉበት ሁኔታ የመለየት፣ የሚገኙበት ስፍራና መጠናቸውን የማጥናትና የመመዝገብ ስራ መከናወኑን  ተናግረዋል፡፡ እምቅ ሃብቶቹ ይበልጥ ለኢኮኖሚ ልማት ውለው ክልሉንና ነዋሪዎችን እንዲጠቅሙ ለማድረግ የማስተዋወቅ ስራም እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንቅስቃሴው ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆንም ኮሚቴው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር የጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ሌላው የኮሚቴው አባል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ተክለሃይማኖት ገብረስላሴ በበኩላቸው ትግራይ ውስጥ ያሉ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች ረዠም ዘመናትን ያስቆጠሩና የህብረተሰቡን ታሪክና ባህል፣ አኗኗር፣ እምነትና የስነ ህንጻ ጥበብ ጥልቅ እውቀትና ክህሎት የሚያጸባርቁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ2 ሺህ 500 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የይሓና የአክሱም መንግስታት የኪነ ህንጻ ጥበባትና ዘመናዊ የእምነትና የባህል ትሩፋቶችን በአብነት አንስተዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አቶ ሙዑዝ ሃይሉ እንዳሉት፣ በክልሉ ያሉትን እምቅ ሃብቶች ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረው ጥረት መልካም መሆናቸውን ተናግረዋል። ''ጉዳዩ ይመለከተናል'' በሚሉ አካላትና በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅንጅት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፋቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሐለፎም በበኩላቸው፣ የትግራይ ክልል እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ባለቤት ቢሆንም እስካሁን ከጥቅም አኳያ ሲመዘን ብዙ እንዳልተሰራበት ተናግረዋል። በባለድርሻ አካላትና የዘርፉ ከፍተኛ ምሁራን የተጀመሩ ስራዎች እምቅ ሃብቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምቹ መዳላድል የሚፈጥሩ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከተለያዩ የክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችና የግል ተቋማት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም