በደቡብ ክልል የፍራፍሬ ልማቱን ከኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ለማስተሳሰር አየተሰራ ነው

65
ሃዋሳ ግንቦት 12/2010 በደቡብ ክልል የፍራፍሬ ልማት ሥራውን ከይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ጋር በማቀናጀት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከመጠናቀቁ በፊት በተለያዩ የክልሉ ዞኖች ለፓርኩ የፍራፍሬ ምርት የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ የፍራፍሬ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለግብርና ማቀነባበሪያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ ትኩረት በመሰጠቱ ከችግኝ ጣቢያ ጀምሮ በአርሶ አደር ደረጃ የችግኝ ዝግጅትና የማልማት ሥራ በልዩ ዕቅድ እየተመራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ "ለፍራፍሬ ልማቱ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ምቹ ቢሆኑም በተለየ ሊተኮርባቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ልማቱን የማስፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው" ብለዋል፡፡ አቶ ጥላሁን እንዳሉት በክልሉ በደጋ ፍራፍሬ 2 ሺህ 770 ሄክታር መሬት በአፕል አየለማ ሲሆን በየዓመቱም ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እየተዘጋጀ ለአርሶአደሩ በመሰራጨት ላይ ነው፡፡ የቆላ ፍራፍሬን በተመለከተም በችግኝ ጣቢያና በአርሶ አደር ደረጃ ከአራት አስከ 20 እግር ችግኝ በመትከል ከሦስትና አራት ዓመት በኋላ ለማድረስ የመንከባከብ ሥራ አየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ልማቱም በዋናነት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዜዴ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። በጨንቻ ወረዳ ኤዞ ቀበሌ በአፕል ልማት ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደር ቶማስ ቶሞሽኬ በበኩላቸው ማሳቸውን በአብዛኛው በአፕል መሸፈናቸውን ገልጸዋል። ከሽያጩ በሚያገኙት ገቢ ለልጆቻቸው የሚያስፈገውን በማሟላት እያስተማሩ ከመሆኑ በተጨማሪ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ የአፕል ችግኝ በብዛት በማዘጋጀት ሥራቸውን ለማስፋትና ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለማቅረብ ተገቢ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ ዳኬ ቀበሌ በአቡካዶ ልማት የተሳተፉት አርሶ አደር ዮሴፍ ጫሌ እንዳሉት ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በፍራፍሬና ቡና በማልማት ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ለማቅረብ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ "በአሁኑ ወቅትም ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚሆን 26 ሄክታር አቡካዶ ተክያለሁ" ብለዋል። በእዚሁ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር መንግስቱ አዲቶ በበኩላቸው ከመልካሳ እርሻ ምርምር ማዕከል የተሻለ ምርት የሚሰጥ የአቦካዶ ዝርያ ቀርቦላቸው የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዝርያው በራሳቸው ችግኝ አፍልተው የማዘጋጀት ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውንም አመለክተዋል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም