የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከመንግስት የተናበበ ድጋፍ ካላገኘ ውጤታማ መሆን አይችልም - ወይዘሮ አዜብ መስፍን

111
አዲስ አበባ መስከረም 28/2011 ሴቶችን በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከመንግስት ጋር በመናበብ ተገቢውን ድጋፍ የማያገኝ ከሆነ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ገለጹ። ፌዴሬሽኑ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚል ባለፉት አስር አመታት ሲተገብራቸው የነበሩ ፓኬጆች ያመጡት ውጤትን በተመለከተ የዳሰሰሳ ጥናት አካሂዷል። በዳሰሳ ጥናቱ ውጤት መሰረት ሴቶች የቁጠባ ባህላቸውን ያሳደጉ ቢሆንም የቆጠቡትን ገንዘብ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር ላይ የማዋል ክፍተት አለባቸው። የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ የመንግስት ተቋማትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል። ''መንግስት ያለውን ትልቅ ዓቅም አቀናጅቶ ሊተገብር እንደሚገባ ያስፈልጋል'' ያሉት ፕሬዚዳንቷ የባለድርሻ አካላቱ መናበብ ባለመቻላቸው የተነሳ በሚፈለገው ልክ ውጤት ሊመጣ ያለመቻሉን ጠቁመዋል። በፌዴሬሽኑ በኩል ሲተገበሩ የቆዩ የሴቶች ተጠቃሚነት ፓኬጆች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የክትትል ፣ ድጋፍና የስልጠና አገልግሎት እንዲያገኙ ሊደረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። ፌዴሬሽኑ በሰራው ስራ በጣም በርካታ ሴቶች ሰርተው ህይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሰው፤ ሴቷ ካለባት ዘርፈ ብዙ ችግር እንድትላቀቅ ለማስቻል የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት መፍጠር እንደሚገባ ወይዘሮ አዜብ ጠቁመዋል። ፓኬጆቹ ያመጡት ውጤትና ያለባቸው ክፍተት ተመዝኖ በቀጣይ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ሴቶችን በዘላቂነት ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራት የሚፈጸም መሆኑንም ወይዘሮ አዜብ ጠቁመዋል። ''ፌዴሬሽኑ ብቻ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከዳር ያደርሳል ማለት በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይቆጠራል'' ያሉት ወይዘሮ አዜብ በጉዳዩ ዙሪያ የቀረበውን ጥናት የሚመለከታቸው አስፈጻሚ ተቋማት ተመልክተው በግኝቱ መሰረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ፌዴሬሽኑ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ያረጋገጡት ወይዘሮ አዜብ እስካሁን የተመዘገቡ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ያሉትን ክፍተቶች ለማረም ዝግጁነት እንዳለ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም