በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ የተማሪዎች ኅብረት አስተዋጽኦ የጎላ ነው

96
ደብረ ማርቆስ መስከረም 27/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ የተማሪዎች ኅብረት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን  የትምህርት ሚነስቴር ገለጸ። በሚኒስቴሩ የሠነ ዜጋና ሥነ ምግባር  ዳይሬክተር አቶ ጌቱ አብዲሳ  34ኛው መደበኛ የተማሪዎች ኅብረት ጉባዔ  በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት ኅብረቱ ለተቋማቱ የመማር ማስተማር ፣የጥናትና ምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውጤታማነት  እገዛ ያደርጋሉ። አስተዳደራዊና የትምህርት  ጉዳዮችን በመከታተል የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ከመፍታት አንጻር የህብረቱ እንቅስቃሴ ቢሆን በጥሩ ጎኑ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት አመታት በአንዳንድ ዩንቨርሲቲዎች  የተከሰቱ ችግሮችን  ከመከላከል ጀምሮ  ሰላማዊ መማር  ማስተማር ሂደት ከመፍጠር አንጻር አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይም የመማር ማስተማሩን ተግባር የሚያደናቅፉ ችግሮች በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዳይፈጠሩ ኅብረቱ ሊሰራ እንደሚገባው የጠቆሙት ኃላፊው፣ለዚህም ሚኒስቴሩ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል። የኢትየጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ አህመድ ሙክታር ኅብረቱ ለተማሪዎች መብትና ጥቅም ከመቆም አንስቶ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል። በተማሪ ኅብረቶችና በሚኒስቴሩ መካከል  ተናቦ ከመስራት አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን አመልክቶ፣ ይህም ችግሮችን ፈጥኖ ከመፍታት አንጻር የራሱ አሉታዊ ሚና ነበረው ብሏል፡፡ በያዝነው የትምህር ዘመን በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ተማሪዎች የዘር፣የሃይማኖትና የብሔር ልዩነቱን አስወግደው እርስ በእርሳቸው ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተግባብተው እንዲኖሩ ጥረት እንደሚደረግም አስታውቋል። ለተማሪዎች መብትና ጥቅም መከበር አጋዥ የሆነ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት የትምህርት ጥራቱም ሆነ  የመማር ማስተማሩን ሂደቱ ስርዓት እንዲኖረው ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው። የደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ የተማሪዎች አስተዳደር ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላልኝ ታምሩ በበኩላቸው የተማሪዎች ኅብረት በዩንቨርሲቲው መኖሩ የመማር ማስተማሩ ሂደት የተቃና እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ በተማሪዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት፣ አብሮነት፣ መቻቻልና መልካም እሴቶች እንዲጠናከሩ እገዛ  እያደረገ መሆኑን  አብራርተዋል። በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ሶስት ቀናት በተካሄደው አገር አቀፍ የተማሪዎች ኅብረት መደበኛ ጉባዔ 160 ሰዎች ተካፍለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም