የጌዴኦ ዞን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት ይሰራል

77
ዲላ መስከረም 27/2011 በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት የተሻለ ገቢ ለማስገኘት በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ ባህል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ገለፀ ፡፡ የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ባለድርሻ አካላትና የዲላ ከተማ ወጣቶች የዞኑን የቱሪስት መስህቦችን ጎብኝተዋል፡፡ ጉብኝቱ በዲላ ከተማ ለቱሪስት አገልግሎት በሚሰጡ ሆቴሎች የተጀመረ ሲሆን፣ቡናን መሰረት ያደረገ የጥምር ደን ግብርና ባለቤት የሆነው የዲላ ዙሪያ ወረዳ መልክዓ ምድር እንዲሁም በቡሌ ወረዳ የሲካ ፏፏቴና ጥንታዊ የእምነት ተቋማት ተጎብኝተዋል ፡፡ የዞኑ ባህል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ እንደገለፁት በዞኑ በርካታ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስዕቦች ቢኖሩም፤ ለቱሪስት ምቹ እንዲሆኑ በማልማት ረገድ ግን ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ፡፡ የጌዴኦ ህዝብ መገለጫ የሆነውን የጥምር ደን ግብርና ዘዴን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ መስህቦችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለማጥናት ፤ ለማልማትና ለመንከባከብ እንዲሁም ለማስተዋወቅ መምሪያው በትኩረት ይሰራል ፡፡ መስህቦቹ ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ እንዲሆኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ተጓዳኝ ተግባራትን በማከናወን ብሎም ባለሀብቶችና ወጣቶችን በዘርፉ በማሰማራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡ ጉብኝቱ በባለ ድርሻ አካላት ላይ ከሚፈጥረው ተነሳሽነት በተጨማሪ ማህበራዊ ትስሰስርን ለማጠናከር ብሎም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት እንዲያስችል በቀጣይ ተመሳሳይ ጉብኝቶች እንደሚካሄዱ ገልፀዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ሞገስ ተሰማ የዞኑ ህዝብ የሚታወቅበት የጥምር ደን ግብርና የአርሶ አደሩ መሬት ለምነቱንና አካባቢው ደግሞ  ሥነ-ምህዳሩን ጠብቆ  እንዲቆይ ያደርጋል ብለዋል ፡፡ ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ በመትከልና በመንከለባከብ ያቆያቸው አገር በቀል ዕፅዋትም በብዝሀ-ሕይወት ጥበቃ ላይ ያላቸው ሚና ጉልህ  መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡ የጥምር ደን ግብርና ህዝቡ ማንም ሳያስተምረው በራሱ ሕይወት ልምድ ያዳበረው ዕውቀት ነው ያሉት አቶ ሞገስ፣ ዕውቀቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍና በመስህብነቱም ለአካባቢው ተገቢውን ኢኮኖሚ  እንዲያመነጭ ጽሕፈት ቤቱ ድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡ ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ በዲላ ከተማ በሆቴል ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አዳነ ጀቦ ጉብኝቱ በአካባቢያቸው ያለውን የቱሪዝም አቅም እንዲረዱ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፣ መስህቦቹ ወደሚገኙበት ሥፍራዎች የመሠረተ ልማት ተቋማት በመዘርጋት ከዘረፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ  ይቻላል ብለዋል ፡፡ ለወደፊቱ የሆቴል አገልግሎታቸውን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል ፡፡ አይቷቸው የማያውቃቸውን ነገር ግን ቢተዋወቁና ጥቅም ላይ ቢውሉ ቱሪስቶችን ለመሳብ አቅም ያላቸው ሥፍራዎች መጎብኘቱን ተናገረው ወጣት ደግነት ኃይሉ ነው፡፡ ወጣት ሰዋገኘው መንግስቱ በበኩሉ በጉብኝቱ ባያቸው ሥፍራዎች እጅግ መደሰቱን ገልፆ፣ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ዘርፉ በሚኖረው የሥራ ዕድል ለይ ለመሰማራት ማቀዱን ተናግሯል ፡፡ ''የላቀ ቴክኖሎጂ ለቱሪዝም ልማት!'' በሚል መሪ ቃል ቀኑን በማስመልከት የተካሄደው ጉብኝት ያዘጋጁት የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ከአገርህን እወቅ ክበባትና ከባለድርሻ አካለት ጋር በመተባበር ነው ፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም