በቡራዩ ከተማ መልካ አቴቴ የኢሬቻ በዓል ዛሬ ተከበረ

158
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ከተከበረው የኢሬቻ በዓል ቀጥሎ ዛሬ በቡራዩ የመልካ አቴቴ ኢሬቻ ተክብሯል፡፡ የመልካ አቴቴ ኢሬቻ በዓል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ ሰላምና ፍቅር የሚማፀኑበት ክብረ በዓል ነው። ለዘመናት የኖረውን ባህላዊ እሴት ጠብቆ በተከበረው የዘንድሮው የመልካ አቴቴ ኢሬቻ በዓል አባ ገዳዎችንና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታዳሚ ሆነዋል። የበዓሉን ጸጥታ ማስከበር ስራ በአባ ገዳዎች ተመርጠው ኃላፊነት የተሰጣቸው ወጣቶች በአግባቡ መወጣት ችለዋል። በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ፣ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ሰው የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል። በዓሉን በመተሳሰብና ከሌሎች ኢትዮጵያን ወገኖች ጋር በመሆን በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት መንፈስ በደስታ እንዳከበሩ ተናግረዋል። በበዓሉ ዘንድሮ በርካታ ታዳሚዎች እንደተገኙ መታዘባቸውንም የሚገልጹት ወይዘሮ አለሚ ኦርዶፋበአሉን በፍቅርና በአንድነት ማክበራቸውን ነው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ከወጣቶች፣ አባ ገዳዎች፣ እና ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ሆነን በጋራ በአሉን ማክበራቸውን ያስረዳው  ወጣት መርጋ ታሪኩ ነው፡፡ በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ያለችው ወይዘሮ ሽቶ በረካ ናት፡፡  ወጣት መርጋ ታሪኩ በበኩሉ በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ወጣቶች የሚሰሩትን ስራ በጥሩ ሁኔታ መቀጠል አለብን ሲል  አባቶቻችንም  እንደተለመደው ልጆችን ስለ ባህላቸው ማሳወቅ ማጠናከር አለባቸው ፡፡  በዓሉ ወደፊት በሁሉም ዘንድ እንዲከበር ለማስቻል የበለጠ መስራት እንደሚገባ የጠቆሙት ታዳሚዎች የመልካ አቴቴ ኢሬቻ በዓል ላይ ከተለያየ ብሔርና ብሔረሰቦች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን በጋራ ማክበራቸውን ተናግረዋል። በዓሉን ለዓለም ለማስተዋወቅ ባህላዊ ገጽታውንና ፋይዳውን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት መከናወን እንደሚኖርበትም የቁመው ወጣት ደረጄ ኩማ ሁሉም በፍቅር በአንድነት ሆነን ሰላማችንን መጠበቅ፣ ባህላችን ማሳደግ፣ ወደ ልማት ስራ መግባት እንደሚያስፈልግ አስረድታል፡፡  በከተማዋ የተከበረው በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር መጠናቀቁን የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደረጀ ባይሳ ተናግረዋል።  በዓሉ በሰላም እንዲከበሩ ላደረጉት ታዳሚዎችና የጸጥታ ሃይሎች ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም