የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ወጪ መቀነስና እርጥበትን ማቆየት እንዳስቻላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ

87
ደብረ ማርቆስ መስከረም 27/2011 የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግዢ ያወጡት የነበረውን ገንዘብ እንደቀነሰላቸውና እርጥበትን ለማቆየት እንዳስቻላቸው የምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ዘንድሮ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች እየተዘጋጀ ነው። አርሶ አደሮቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት በአካበቢያቸው የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ፤ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የሚገዙበትን ወጪ በመቀነስና የአፈርን እርጥበት ጠብቆ ለማቆየት አስችሏቸዋል። በአነደድ ወረዳ የእነችፎ ቀበሌ አርሶ አደር ገድፍ ይርጋ  በአካባቢያቸው የእፅዋትና ሰብል ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የሚያዘጋጁት ማዳበሪያ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ያወጡት የነበረውን ስምንት ሺህ ብር ወደ 2ሺህ500 ብር ዝቅ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በመኸር የምርት ወቅትና በመስኖ ለሚያለሙት ሰብል 40 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጀተው መጠቀማቸው አስታውቀዋል። የጎዛምን ወረዳ የቸር ተከል ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አላምር አካሉ በበኩላቸው በየዓመቱ ከ10 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያዘጋጁ እንደሚጠቀሙ አመልክተው፤በዚህም  የመሬትን ርጥበት ይዞ ለማቆየትና ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በበለጠ ምርታማነቴን እንድጨምር አድርጎኛል ብለዋል። በዓመት እስከ 60 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በመጠቀም ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ መጠቀም ማቆማቸውን የገለጹት ደግሞ የማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አያሌው ታፈሰ ናቸው። በተለይም በመስኖ በሚያለሙት ግማሽ ሄክታር መሬት የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚያካሂዱት  በተፈጥሮ ማዳበሪያ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢአለ አለኽኝ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘጋጅቶ የመጠቀም ባህሉ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት 167 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል። የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለበጋ መስኖና ለመኽር እርሻ ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል።እስካሁንም  ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ለሚሳተፉ  70 ሺህ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ  እንደሚያደርጉላቸውም አቶ እምቢአለ አሰረድተዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም