ለህዝቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ወጣት አመራሮች ገለጹ

74
ሐዋሳ መስከረም 27/2011 የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለህዝቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባዔ የተሳተፉ ወጣት አመራሮች ገለጹ፡፡ የኢህአዴግና የእህት ድርጅት ጉባዔዎችን ተከትሎ ወደ አመራርነት የመጡት ወጣት አመራሮች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮችን በማቃለል ለህዝቡ ጥያቄዎች ፈጣን መልስ ለመስጠት እንተጋለን ብለዋል፡፡ በሲዳማ ዞን የደዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘነበ ለገሰ ወጣቱ አመራር የወጣቱን ሥነ ልቡና የሚረዳና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹን በመፍታትና ለጥያቄዎቹ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠልም ወጣቱን ለአመጽ የሚያስነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን መሙላት እንደሚገባ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ጉባዔው በአመራር ሂደት ያጋጠሙ ብልሽቶችን ማረም ላይ ትኩረት በማድረግ አዳዲስ ሃሳቦችን አፍልቆ ለመምራት ቃል የተገባንበት ወቅት እንደነበር አመልክተዋል፡፡ የአማሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አብደላ ጉባዔው በለውጥና በለውጡ ፈተናዎች ውስጥ መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፣ የለውጡን ፈተና በመቀነስ የተገኙ መልካም እድሎች ለማስቀጠል የአመራር መተካካቱ አስፈላጊ ነበር ብለዋል፡፡ "ወደ አመራርነት የመጣን አዲስ ወጣት አመራሮች ኢትዮጵያ የወጣት አገር መሆኗን ተገንዝበን በተለይም የወጣቱን የኢኮኖሚ ጥያቄ ለመመለስ ልንሰራ ይገባል'' ሲሉ አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ በጉባዔው የተቀመጠውን አቅጣጫ መነሻ በማድረግ በምጣኔ ሀብት፣በአስተዳደር እርከኖችና የፍትህ አካላት ሪፎርም ላይ ትኩረት በማድረግ የህዝብን ጥያቄ በመመለስ የተጀመረውን ለውጡ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ መዲና ሞላ ጉባዔው በብቃት የሚመሩ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣቱ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጉባዔዎች የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በህግ የበላይነት፣ በወጣቶች ስራ አጥነትና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጉባዔው የተላለፉ  ውሳኔዎች ተገቢ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ መዲና በየአካባቢው የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት፡፡ ሴቶች በማህበራዊ ዘርፍ የሚደርስባቸውን ጫና በመቀነስ የአመራር ሰጪነት ሚናቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ወይዘሮ መዲና አሳስበዋል፡፡ ላለፉት ሶስት ቀናት በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛ የኢህአዴግ  ድርጅታዊ ጉባዔ በርካታ አዳዲስ አመራሮች የተሳተፉበት ነበር፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም