በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን ማጎልበት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

60
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ በተለይ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል አዳማ ከተማ በ140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ በይፋ ተመርቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ የአገሪቷን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ልማትን ማፋጠንና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲስፋፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የውጭ ኢንቨስተሮች ብቻ ሳይሆኑ የአገር ውስጥ ባለሀብቶቸም በዘርፉ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል። መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ድህነትን ለመታገልና የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት እንዲይዝ ለማድረግ ሕጎችና አሰራሮችን በተገቢው መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። በቀጣይ ኢትዮጵያ ሰላሟ የተጠበቀ የልማትና የቱሪስት መስህብ እንድትሆን ያለውን መሻት ለማሳካት በቁርጠኝነት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታ በተሟላ መንገድ እንዲሳካ ከመንግስት ባልተናነሰ ሁኔታ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አርሶ አደሮችንም አመስግነዋል። ወጣቶች ልማቱን በማጠናከር ረገድ በአንድነትና በኃላፊነት ስሜት በሙሉ ልብ ወደ ልማት ፊታቸውን እንዲያዞሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ኢንዱስትሪያል ፓርኩ በተገጠመለት ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ በቀን እስከ 11ሺ ሜትሪክ ኩብ በማጣራት ምንም ዓይነት ቆሻሻ ወደ አካባቢው እንዳይወጣ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል። ከሀዋሳና ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልምድ ተቀምሮ የተገነባው ፓርክ በዋናው የኢትዮ ጅቡቲ የኤክስፖርት ኮሪደር ይገኛል። ትላልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የሚስተናገዱበት  መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አጠቃላይ በሁለት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በመንግስትና በአልሚዎች በተለያዩ ምዕራፎች የሚገነባ ነው። ኢትዮጵያ በ2012 በድምሩ 30 ኢንደስትሪ ፓርኮች ይኖሯታል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም