በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ከ14 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ማህበራዊ አገልግሎት ሰጡ

965

ፍቼ መስከረም 27/2011 ባለፈው ክረምት በበጎ ፈቃድ  አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ከ14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር  በላይ የሚገመት  ማህበራዊ አገልግሎት  መስጠታቸውን  በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት  አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ  የወጣቶች አደረጃጀትና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መኮንን ግዛው ለኢዜአ እንደገለጹት በአገልግሎቱ የተሰማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና የአካባቢው 79 ሺህ ወጣቶች በዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች አገልግሎቱን ሰጥተዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ  ለ27 ሺህ  የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እገዛ አድርገዋል፡፡

እንዲሁም ከ355 ሺህ በላይ  ችግኞችን በተራቆቱ አካባቢዎች ተክለዋል፡፡

ለአቅመ ደካሞችና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት የመስራትና የመጠገን እንዲሁም  የአርሶ አደሮች ማሳን በማረስ እገዛ አድርገዋል ።

ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙያዊ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ፤ የትምህርት ቤቶችን አጥር በማጠርና በአካባቢ ጽዳት በመሰማራት አገልግሎቱን ሰጥተዋል፡፡

በወጣቶቹ የተከናወነው ሥራ አገልግሎቱ የኅብረተሰቡ ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግና በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ባለፈው ዓመት የታየው በጎ ተግባር በያዝነው ዓመት  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በክረምት በጐ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በደም ልገሳና በትራፊክ ደህንነት ሥራ የተሳተፈው የፍቼ ከተማ ቀበሌ ዐ1 ነዋሪው ወጣት ደሣለኝ ጉርሜሣ  ለኅብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠቴ  የህሊና እርካታ እንዲሰማኝ አድርጓል ብሏል።

ወጣቶች ጊዜያቸውን አገልግሎቱን በመስጠት ቢያሳልፉ ለቤተሰብም ሆነ ለአገር  ፋይዳው የጎላ መሆኑን ወጣቱ ተናግሯል።

በአገልግሎቱ የተሳተፈው ወጣት ገመቺስ ወርዶፋ በበኩሉ በአገልግሎቱ ያደረገው ተሳትፎ  ለቀጣይ ስራ የተነሳሽነት መንፈስን ፈጥሮልኛል ብሏል፡፡

በቀጣዩ  የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትምህርትና ልምዱን በማቀናጀት ለአካባቢው ነዋሪዎች አርአያነት ያለው ሥራ ለማከናወን እንደሚዘጋጅም አስታውቋል።

የግራር ጃረሶ  ወረዳ ወርጡ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የ73 ዓመት አዛውንት አቶ መርጊያ ቱሉ በበጐ ፈቃደኛ ወጣቶች የእርሻ መሬታቸው እንደታረሰላቸው ተናግረዋል፡፡ወጣቶቹ ወደ ገጠር ዘልቀው በመግባት አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን መርዳታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ያከናወኑት በጎ ተግባር መጠናከር እንዳለበት የጠቆሙት አዛውንቱ  አስተያየት ሰጪ፣የወጣቶቹን በጎ  ሥራ መንግሥትና ሕዝብ ሊያበረታታው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ወጣት ዘውዱ አሰፋ  አገልግሎቱ  በአንዳንድ ወጣቶች የሚታየውን የተስፋ መቁረጥ፣ የሥራ ባሕል ማጣትና ለተለያዩ ሱሶች የመገዛት አዝማሚያ በመቀነስ የአስተሳሰብ ለውጥና የሥራ ተነሳሽነት ያመጣል ሲል ተናግሯል፡፡