የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዘርፉ ልማት ትክክለኛ መስመር መያዙ ማሳያ እንደሆነ ገለጹ

2294

አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ  የኢንደስትሪ ፓርኮችን ቁጥር ከፍ ከማድረግ ባሻገር የኢንደስትሪ ልማት ትክክለኛ ፈር ይዞ እየተጓዘ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ተናገሩ።

በ4ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ እንደተናገሩት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ ፋብሪካዎችን በአንድ ጣሪያ ውስጥ አሰባስበው የያዙና አስፈላጊ የመገልገያ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ዘመናዊ ማዕከላት ናቸው።

ፓርኮቹ ኢንቨስተሮች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ በተመቻቸ የኢንደስትሪ አካባቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምረቻዎቻቸውን ተክለው ወደስራ ለመግባትና ምርቶቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም የኢንደስትሪ ፓርኮችን ቁጥር ከፍ ከማድረግ ባሻገር የዘርፉ ልማት ትክክለኛ ፈር ይዞ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረለትና እያደገ መሆኑን የሚያበስር መሆኑንም ተናግረዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን የሚያመርት ብቸኛ የልማት ማዕከል መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።

”ፓርኩ ለትራንስፖርት ምቹ በሆነ ቦታ መገኘቱ ወሳኝ ያደርገዋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት እንዲሁም አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ፓርኩ በሙሉ አቅም ሲንቀሳቀስ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥርና ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀ፣ ከቀልጣፋ አሰራር ጋር የተዛመደና ለምርትና ምርታማነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የስራ ዕድል የሚፈጥርና የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚካሄድበት ማዕከል በመሆን ትልቅ ድርሻ የሚያበረክት ተቋም እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ወጣቶች የኢንዱስትሪ ፓርኩ በሚፈጥረው የስራ እድል ከመሳተፍ ባሻገር በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በመደራጀት ለፓርኩ ግብዓት ማቅረብ እንዳለባቸውም ገለፀዋል።

”የኢንዱስትሪ ልማት የአገሪቱን ገፅታ ለመቀየርና የተደላደለ ህይወት የሚመራ ዘመናዊ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችል የእድገት አቅጣጫ ነው” ያሉት አቶ ለማ ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በሁሉም መስክ ራሷን የቻለች አገር እውን ለማድረግ ወሳኝ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

መንግስት ግብርና እየዘመነ ምርትና ምርታማነቱ በላቀ ደረጃ እንዲያድግና በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የመሪነት ሚና ለኢንዱስትሪው እየለቀቀ እንዲሄድ ለማስቻል በፖሊሲና ስትራቴጂ የተደገፈ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጥኖ እንዲያድግና በኢኮኖሚ ውስጥ ተገቢ ድርሻውን እንዲያበረክት ለማስቻል የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ልማት ላይ እንዲሰማሩ በተለያየ መንገድ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ተጨባጭና ፍሬያማ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ነው አቶ ለማ የተናገሩት።