የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገጠመለት የፍሳሽ ማጣሪያ 11ሺህ ሜትሪክ ኩብ ያጣራል

182
አዲስ አበባ 27/2011 የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተገጠመለት አለም አቀፍ የፍሳሽ ማጣሪያ መሳሪያ በቀን 11ሺህ ሜትሪክ ኩብ ማጣራት ይችላል ተባለ። ይህ የተነገረው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምረቃ ስነ ስርአት ሲካሄድ ነው። በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ አካባቢን ከብክለት ለመከላከል የሚያስችል አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ መሳሪያ ተገጥሞለታል። ፓርኩ በተገጠመለት ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ በቀን እስከ 11ሺህ ሜትሪክ ኩብ በማጣራት ምንም አይነት ቆሻሻ ወደ አካባቢው እንዳይወጣ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም እስከ 85 በመቶ ውሃ የመቆጠብ አቅም ሲኖረው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርአትም ተበጅቶለታል ነው የተባለው። በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት ከታቀደው 2ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ዛሬ የተመረቀው 100 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ። በተጨማሪ በሁለት የውጭ አልሚዎች በ112 ሔክታር መሬት ላይ ግንባታቸው እየተከናወኑ የሚገኙ ፓርኮች እንደሚገኙ ወይዘሪት ሌሊሴ ገልጸዋል። እነዚህ ፓርኮች ወደ ስራ ሲገቡ ተጨማሪ የስራ እድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ የከባድ ማሽነሪ ማምረቻና መገጣጠሚያ ላይ ትኩረት ያደረጉ በ122 ሔክታር ላይ ተጨማሪ ግንባታዎችን ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።   የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ክሊኒክ፣ አደጋ መከላከያ፣ የገበያ ማዕከል፣ ካፌና ሬስቶራንትን ጨምሮ አንድ ከተማ ሊያሟላ የሚችለውን መሰረተ ልማቶች አሟልቶ መያዙ ተነግሯል። አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኤክስፖርትን መሰረት በማድረግ ጨርቃ ጨርቅና ማሽነሪ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። በፓርኩ ለሚገቡ የአንድ ማዕከል አገልግሎትና በእውቀት የሚመራ ኦፕሬሽንና ማኔጅመንት አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል። ኢንዱስሪ ፓርኩን መርቀው የሚከፍቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው። በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይ ተገኝተዋል።                                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም