በ140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምእራፍ ሥራ ሊጀምር ነው

87
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በ140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምእራፍ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ እየተመረቀ ነው። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 19 የማምረቻ ህንፃዎችን ይዟል። ከፓርኩ ጋር የተያያዙና መንገድን ጨምሮ የተለያየ መሰረተ ልማት አውታሮችን ያካተተ ግንባታም ተከናውኗል። በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ዓለም አቀፍ አውቅና የተቸራቸው የተለያዩ ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ የማምረት ሥራ ለመጀመር ከወዲሁ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል። ፓርኩ በጠቅላላው 20 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን በየዓመቱም ከ38 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በ2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተለያዩ ምእራፎች መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ አልሚዎች የሚገነባ ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር ነው። ኮርፖሬሽኑ ካስገነባው የመጀመሪያው ምእራፍ ከእነዚህ የማምረቻ ህንፃዎች በተጨማሪ ዉል ቴክስታይልንና ኪንግዶም ሊነን ኢትዮጵያ የተሰኙ ትላልቅ የቻይና ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ ተመሳሳይ ህንፃዎች ግንባታ በማካሄድ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም