ለህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በማይሰጡ አመራሮች ላይ ተገቢው ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል---የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች

99
ጋምቤላ  መስከረም 26/2011 በህዝቦች መካከል ግጭትን የሚፈጥሩና ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ የማይሰጡ አመራሮች ላይ ተገቢ የማስተካከያ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ገለጹ። ወጣቶቹ በከተማው የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከጸጥታ አካላትና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትላንት ተወያይተዋል። ከውይይት ተሳተፊዎች መካከል ወጣት ኡሞድ ኡቻላ በሰጠው አስተያየት በወጣቶች መካከል ጊዜያዊ አለመግባባት ሲፈጠር ለጥቅማቸው ሲሉ የክልሉ ጸጥታ እንዲደፈርስና ህዝቦች እንዲጋጩ እያደረጉ ያሉት አመራሮች ናቸው። እንደ ወጣቱ ገለፃ በየዓመቱ ለክልሉ የሚመደበው የልማት በጀት ወጣቱ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ እየዋለ ባለመሆኑ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። "ወጣቱ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የማይፈታ አመራር ከኃላፊነቱ ሊነሳ ይገባል" ያለችው ደግሞ ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት አባንግ ኮመዳን ናት። ወጣቱ የሚፈልገው ስልጣን  ሳይሆን በሰላም የመኖርንና የልማት ተጠቃሚ መሆንን ነው በማለትም ተናግራለች። ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ኡሞድ አላር በጋምቤላ ከተማ የተፈጠረው የሰላም ችግር ወደ ነበረበት ለመመለስ የሀገር መከላከያና ፈዴራል ፖሊስ የጸጥታ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። "በተለይም በከተማው የተፈጠረውን የሰላም ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ህጋዊም ሆነ ህጋዊ ያልሆነ የጦር መሳሪያን የማስፈታት ሥራ ሊሰራ" ይገባል ሲል ተናግሯል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ በተለይ በክልሉ የተጠለሉት የደቡብ ሱዳን ሰደተኞች የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆናቸው የስደተኞች አያያዝ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ ከመድረኩ አወያዮች መካለል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ እንደተናገሩት በወጣቶቹ የተነሱት የልማት፣ የመልካም አስተዳዳርና የተጠቃሚነት ጥያቄች አግባብነት ያላቸውና ወጣቱን ሊያስቆጡ የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ጥያቄዎቹ በወቅቱ ምላሽ ካለማግኘታቸው ጋር ተያይዞም  የሰላም ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆኑ ተናግረዋል ። የተነሱት ጥያቄዎች ስርዓቱን ጠብቆ በአግባቡ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ወጣቱ ትግስት ሊያደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የ12ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጄንራል ብርሀኑ ጥላሁን በበኩላቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት በከተማው የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ከወጣቱ የጎላ አስተዋጽኦ ይጠበቃል። ግጭቶችን ሊያባብሱ የሚችሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪዎችና ስለታማ ነገሮችን ለማስፈታት ዕቅድ መያዙን ጠቁመው ለስኬታማነቱ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ስደተኞች የክልሉ የጸጥታ ችግሮች እየሆኑ መጥተዋል በሚል የተነሳው ጥያቄ አግባብነት እንዳለው ጠቁመው በስደተኞች አያያዝ ላይ የሚመለከተው አካል ማስተካካያ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም