የኢህአዴግ ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

83
ሀዋሳ መስከረም 26/2011 ለሶስት ቀናት በሃዋሳ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ጉባኤው ያለምንም የጸጥታ ችግር በስኬት ተጠናቋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራልና የክልሉ ፖሊስ አባላት፣ የፌዴራል መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለጉባኤው በሰላም መጠናቀቅ ያበረከቱት አስተዋዕኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል ። በጉባኤው ኢህአዴግ ከምንም ጊዜ በተለየ ሁኔታ አንድ ሆኖ የወጣበት እንደነበርና የጉባኤው ተሳታፊዎችም ለህግ መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩበት እንደነበር አስታውሰዋል ። ኮሚሽነሩ እንዳሉት ጉባኤው በሀገሪቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከብር የሚያስችሉ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የተነሳውን ግጭት አስመልክቶ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ የተጋነነ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። በአካባቢው ዞን የመሆን ጥያቄ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉና አልፎ አልፎ ከሚነሳ ሁከት ባለፈ የተባለው ነገር ከእውነታው የተጋነነ መሆኑን ጠቁመዋል ። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ የገለፁት ኮሚሽነሩ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር የመከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ በጋራ መሰማራታቸውን ገልጸዋል ። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ  በአካባቢው የታጠቁ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ እየተከናወነ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም