ሰንደቅ ዓላማ የማንነት መገለጫ እንጂ የመለያያና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም-ነዋሪዎች

135
አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 ሰንደቅ ዓላማ ለሁሉም ህዝቦች እኩል ትርጉም ያለው የሉዓላዊነትና የማንነት መገለጫ እንጂ የመለያያና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለሰንደቅ ዓላማው የተከፈለለትን መስዋትነት በማሰብ ለአገሪቱ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም ተናግረዋል። ሰንደቅ ዓላማ የአንድ አገር ኩራትና የህዝቦቿም የማንነት መገለጫ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ዘመን ተሻጋሪ የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በሰንደቅ ዓላማ ስም በጐም ሆነ መጥፎ ተግባራት በተፈፀሙባቸው ዘመነ መንግስታት ህዝቡ ለሰንደቅ ዓላማ ያለውን ፍቅርና ክብር ሲገልጽ ኖሯል። በዚህም ሰንደቅ ዓላማውንም የአንድነት ምልክት አድርገው እንደሚያዩትና ትልቅ ክብር እንደሚሰጡት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና በቅርቡ በአገሪቷ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ተያይዞ አላስፈላጊና አግባብነት የሌላቸው ግጭቶች ተፈጥረው እንደነበር የሚታወስ ነው። በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነትና የማንነት መገለጫ በመሆኑ የመለያየትና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም ይላሉ። ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና ማንኛውም አካል ሃሳቡን በውይይትና በሰለማዊ መንገድ መግለጽ እንዳለበትም ነው ነዋሪዎቹ የሚገልጹት። አቶ ሰውነት መስፍን እንደተናገሩት  ሰንደቅ ዓላማ ከአንድ ከሉዓላዊነት ከተረጋገጡበት አገር በስተጀርባ ያለ የማንነት አሻራ ነው እና አንድ አገርና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለየብቻቸው ናቸው ብለዋል ሌላው የከተማው ነዋሪ  ወጣት ባምላክ አለቤ ሰንደቅ ዓላማን ከአገሬ ኢትዮጵያ አሳንሼ አላያትም ሰንደቅ ዓላማ  ማለት የአገሬ መገለጫ፣ ክብሬ፣ ማንነቴን የምገልጽበት ነው ብሏል ኢትዮጵያን በተለያዩ ሰንደቅ ዓላማ መወከል አንችልም ፤ ስለ ባንዲራ ስናስብ ከስሜታዊነት በዘለለ መልኩ ልናስብ ይገባል ሲልም ጨምሮ  ተናግሯል ወይዘሮ መድሐኒት መዝገቡ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ ለሁሉም ሰው እኩል ትርጉም  ያለው ሲሆን ሰንደቅ ዓላማውን ማክበር ማለት  አገራችንን ማክበር ማለት ነው ብለዋል፡፡ "ሰንደቅ ዓላማ ብዙዎች እናትና አባቶች ደማቸውን  እንዳፈሰሱበት  ትልቅ ክብር እንዳለውና  ለአገርም ኩራት መሆኑ  የሚታወቅ ነው፡፡ ባንዲራችን እራሱ ሲያዩት እኮ ደስ ይላል ብናከብረውና ክብሩ  አንደበፊቱ  ቢሆን ደስ ይለኛል።" ያለቸው ደግሞ የከተማው ነዋሪ የሆነቸው   መጽሔት  አስታርቄ  ናት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል መከበር የጀመረው በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር ወቅት ላይ ሲሆን የዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ በዓሉ በየዓመቱ በጥቅምት ወር በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበርም ይደነግጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም