የመዲናዋ የግንባታ ዘርፍ ፈጣን ዕድገት ለመንገድ ሀብት ብክነት ጦስ ሆኗል

69
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 ከአገር ርዕሰ መዲናነት አልፋ የአፍሪካ ሕብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የሚስተዋለው የሕንጻ ግንባታ ዘርፍ ፍጥነትና ስፋት ሲነሳ “ከተማዋ ፈርሳ እየተሰራች ነው’’ የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ። በመዲናዋ የሚስተዋለው ከፍተኛ የህንጻ ግንባታ በአዲስና ነባር የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱ ግን ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ ሆኗል። የትራንስፖርቱን ዘርፍ ለማሳለጥ የተዘረጉ በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ከግንባታ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ብክነት እየተዳረጉ እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ይገልጻል። ከተማ አስተዳድሩ እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 300 ኪሎ ሜትር  የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ከ40 እስከ 50 ቢሊዮን ብር መድቦ ነባር መንገዶችን ለማደስና አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የባለስልጣኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና የመንገድ ፕሮጀክቶች በቴሌ፣ በውሃና ፍሳሽ እንዲሁም በመብራት አገልግሎት ተቋማት ከሚደርሱባቸው ጉዳቶች በተጨማሪ በህንጻ ግንባታ ግብዓቶች ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ፤ የመንገድ ሀብት አጠቃቅም ሊታሰብብት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልጻል። በባለስልጣኑ የማዕከላዊ አዲስ አበባ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በላይ ወልደአረጋይ እንደሚሉት፤ ከመንገድ ሀብት ብክነት መንስኤዎች መካከል የግንባታ ተረፈ ምርቶች አንዱ ነው። የሕንጻ ግንባታ ተቋራጮች ወይም አልሚዎች የግንባታ ተረፈ ምርትና ግብዓቶችን በተሽከርካሪም ሆነ በእግረኛ መንገድ ላይ ማስቀመጥ እንደማይችሉ የከተማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ይገልጻል። የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አለቃ እንደሚሉት ባለስልጣኑ የግንባታ ፈቃድ መስጠት፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ በመጨረሻም የመጠቀሚያ ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት አለው። ባለስለጣኑ ግንባታው ከሚካሄድበት ስፍራ ውጭ በመንገድም ሆነ በትርፍ ቦታ ግብዓት የማስቀመጫ ፈቃድ መስጠት እንደማይችል ገልጸዋል። ነገር ግን በመንገድ ላይ ለማስቀመጥ የመንገዶች ባለስልጣንን ፈቃድ እንዲሁም በመሬት ባንክ በኩል በጊዜያዊ ሊዝ የግብዓት ማስቀመጫ ሊፈቀድ እንደሚችል ይናገራሉ። በከተማዋ የሚስተዋለው ህገ ወጥ ተግባር ታዲያ ለምን ይፈጸማል የሚለውን ጥያቄ በከተማ አስተዳድሩ የመቆጣጠር ኃላፊነት ለተሰጠው የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት አቅርበናል። የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር አሳዬ አምባዬ በመንገድ ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ግንባታ ግብዓቶች ለመንገድ ሀብት ብክነት ብቻ ሳይሆን ለእግረኛና ለትራንስፖርት ፍሰቱም አዋኪ ሆነው መቀጠላቸውን አልሸሸጉም። ደንብ ማስከበር  ጽሕፈት ቤቱ ብቻውን ሕገ ወጥ ተግባሩን መከላከል እንደማይችል ገልጸው፤ የመንገዶች ባለስልጣንን ጨምሮ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል ፅህፈት ቤቱ ግንዛቤ እየፈጠረና የቅጣት እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል። የመዲናዋን የመንገድ ሀብት ብክነት ለመከላከል ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ በህግ ክፍሉ ክስ እየመሰረተ የፈረሰው ንብረት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እንደሚያደርግ አቶ በላይ ገልጸዋል። በሌላ በኩል “ከደንብ ማስከበር ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይሁንና በደንብ አስከባሪዎች በኩል ተከታታይነት ያለው ጥበቃና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል። ተቀናጅቶ አለመስራት የዘርፉ ትልቅ ችግር ነው የሚሉት አቶ መለሰ በበኩላቸው፤ተቋማቱ በቅንጅት መስራት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም