አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት ጉባኤዎች እንዲወከሉ ተወሰነ

204
ሀዋሳ መስከረም 26/2011 አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ምክር ቤት ጉባኤዎች ውስጥ እንዲወከሉ ተወሰነ። ኢህአዴግ በሃዋሳ ከተማ ለሦስት ቀናት ባካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ቀጣይ የድርጅቱን የለውጥ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል። የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንደገለጹት አጋር ድርጅቶች ከተያዘው ዓመት ጀምሮ አምስት ሥራ አስፈፃሚዎች በኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲሁም የክልል ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲ  ሊቀመናብርት በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ተወክለው ያለ ጽምጽ ይሳተፋሉ። አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት እንዲሳተፉ መደረጉ ልምድ ለመውሰድ እንደሚያስችላቸው የገለጹት አቶ ፍቃዱ በቀጣይ ሙሉ በሙሉ አባል የሚሆኑበትን መንገድ አጥንቶ እንዲያቀርብ የኢህአዴግ ምክር ቤት መወከሉን ተናግረዋል። የዜጎችን የአገልግሎት እርካታ ለማምጣት ሲባልም ሁሉም የመንግስት ተቋማት ሙሉ በሙሉ በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል። በተመሳሳይም የጸጥታ፣ የፍትህና የደህንነት ዘርፉም ልዩ ጥናት ተደርጎ ለውጥ የሚደረግበት መሆኑን አመልክተዋል። "የህግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት ይሰራል"ያሉት ቃል አቀባዩ ከአሁን በኋላ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ በትዕግስት እንደማይታለፉ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል። ከጎረቤት ሃገራት ጋር የተጀመረው የዲፕሎማሲ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደረግ ገልጸው ኢትዮጵያ በኢህአዴግ መሪነት የቀጣናውን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ የአፍሪካን ልማትና አንድነት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣ መወሰኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ ኢህአዴግ የሚከተለው የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመርም እንዲቀጥል መወሰኑን ገልጸው የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በትምህርት ዝግጅታቸውና በህዝብ ተቀባይነታቸው እየታዩ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ጠቁመዋል። በቀጣይ የሚደረገው ምርጫም ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ አደረጃጀቶቹ በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም