እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ተስማማች

140
አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 እንግሊዝ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና ኢንቨስትመንት መሰረተ ልማት የሚውል 6 ነጥብ 31 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠት ተስማማች። ስምምነቱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በአፍሪካ የእንግሊዝ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስስ ሃሪት ባልድዊን መካከል ዛሬ ተፈርሟል። ኢትዮጵያ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያከናወነች ያለውን ተግባር የሚያግዝና ለኢንቨስትመንት መሰረተ ልማትና አቅም ግንባታ የሚውል 176 ሚሊዮን ዩሮ ወይም የ6 ነጥብ 31 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ነው ስምምነት የተደረገው። ከዚህ ውስጥ 110 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 3 ነጥብ 94 ሚሊዮን ብር ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም 66 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 2 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ለኢንቨስትመንት መሰረተ ልማት የሚውል ነው። ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት የተደረገው ድጋፍ በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ሶማሌ ክልሎች በቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ጨምሮ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ እንደገለጹት የድጋፍ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በትምህርት ጥራትና ኢንቨስትመንት መስኮች እየሰራች ላለው ተግባር የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተደረገው ድጋፍ በታዳጊ ክልሎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት፣ ጠንካራ የትምህርት አመራሮችን  ለመፍጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ይውላልም ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ቀሪው 66 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 2 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ኢንቨስትመንትና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙያዊ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚውል ነው። የተፈረመው የድጋፍ ስምምነት የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያሳይ በመግለጽም ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታከናውነው ሁሉን አቀፍ ልማት እንግሊዝ ድጋፏን እንድትቀጥል ጠይቀዋል። ሚስስ ሃሪት ባልድዊን በበኩላቸው የኢትዮጵያን ፈጣን እድገት ለማሳካት እንግሊዝ በትብብር ትሰራለች ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢኮኖሚው መስክ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት እውን እንዲሆን ሙያዊና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል። እንግሊዝ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም ታደንቃለችም ብለዋል። የተደረገው ድጋፍ አንድ ሚሊዮን ህጻናት የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙና 125 ሺህ መምህራን ሙያቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛል ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም