በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በኦፋ ወረዳ በተከሰተ ወባ መሰል በሽታ ዘጠኝ ሰዎች ሞቱ

71
ሶዶ መስከረም 25/2011 በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በኦፋ ወረዳ በተከሰተ ለጊዜው ምንነቱ ባልተለየ ወባ መሰል በሽታ ዘጠኝ የአካባቢው ነዋሪዎች መሞታቸውን የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወርቁ እንደገለጹት ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአካባቢው በተከሰተው በዚህ ወባ መሰል በሽታ ከሞቱት ባለፈ 16 ሰዎች በህክምና ላይ ይገኛሉ። ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ህመም፣ የዓይን ቀለም በመቀየር በዓይንና በአፍንጫ የደም መፍሰስ፣እንዲሁም ጥቁር ዓይነ ምድርና ተመሳሳይ የህመም ምልክት የታየባቸው ግለሰቦች በጤና ጣቢያዎች በመበራከታቸው ወባ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በወረዳው ቡሻና ኮዶ ቀበሌዎች የተከሰተውን በሽታ ምንነት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል ናሙና ተወስዶ ምርመራ መካሔዱን ጠቁመው ውጤቱ እስከሚደርስ ከምልክቱ በመነሳት የኬሚካል ርጭትና የወባ መከላከል እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። የዞኑ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ፋንታ ከመስከረም 20/2011 ዓ.ም ጀምሮ መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸው ወደ አካባቢው ባለሙያ በመላክ በተደረገው ማጣራት የተከሰተው በሽታ ከቢጫ ወባ ጋር ተመሳሳይ ምልክት እንዳለው ጠቁመዋል። የበሽታው ምንነት ለማረጋገጥ ናሙናው ወደ ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መላኩን ያስታወሱት ኃላፊው ለተጨማሪ ምርመራም በኢንስቲትዩቱ በኩል ወደ ውጭ ሃገር መላኩን አስታውቀዋል፡፡ “የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በሽታው በወረርሽኝ መልክ እንዳይስፋፋ  በትኩረት እየተሰራ ነው” ብለዋል። በኦፋ ወረዳ ገሱባ ጤና ጣቢያ በበሽታዉ ተጠቅተው ህክምና ላይ ያሉ ግለሰቦችን የጎበኙት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም አላኖ “በሽታውን ከመከላከል አንጻር የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል። በሽታው የወባ ምልክት ያለው መሆኑን ማየታቸውን የገለጹት ኃላፊው የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የመከላከሉ ስራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስረድተዋል። ለዚህም ቢሮው ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር በመሆን ክትትል እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አብርሃም እናቶችና ህጻናት በበሽታው እንዳይጠቁ በአጎበር ስርጭትና በክትባት የቅድመ መከላከል ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ህብረተሰቡ አጎበር በመጠቀም በሽታውን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ገልጸው የህመም ስሜት ሲኖርም በፍጥነት በአቅራቢያ ወደ ሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ እንዲያደርግ አሳስበዋል። የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ከክልሉ ጤና ቢሮና ከዞኑ ጤና መምሪያ የተወጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም