በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ24 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በማሾ ሰብል ተሸፍኗል

162
ደብረ ብርሃን መስከረም 25/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ማሾ ሰብል በ24 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ መልማቱ ተገለጸ፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመዉ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኖቹ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘውና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርገው የማሾሰብል እየለማ ነው። ከዞኖቹ 202 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎም ይጠበቃል። በዞኑ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም 19 ሺህ 302 ሄክታር መሬት መልማቱን የተናገሩት ባለሙያው፣ይህም 15 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ከተያዘው ዕቅድ በላይ መሆኑን አስረድተዋል። የአርሶ አደሮቹ ምርቱ በገበያ ያለውን ተፈላጊነትና የክረምቱ ዝናብ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀማቸው ነው ብለዋል፡፡ የአየር ንብረታቸው ተስማሚ በሆኑ የዞኑ 18 ወረዳዎች በመልማት ላይ ያለው ሰብል  በጥሩ ይዞታ  ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል። የማሾ ሰብል በስፋት ከሚመረትባቸው ወረዳዎች መካከልም ቀወት፣ በረኸት፣ ሽዋሮቢት፣ ሞረትና ጅሩ፣ እንሳሮና መራቤቴ ይገኙበታል። በተመሳሳይ መልኩ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ገለቱ እንደገለጹት በዞኑ አምስት ሺህ 208 ሄክታር መሬት በማሾ ሰብል እየለማ ነው፡፡ ሰብሉ በገበያ ተፈላጊ በመሆኑም የአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎትም እየጨመረ መጥቷል፡፡ አርሶ አደሮች በባለሙያ እንዲታገዙና የግብርና ቴክኖሎጅዎችን እንዲጠቀሙ ተደርጓል ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም  ከ67 ሺህ 700 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ በቀወት ወረዳ የየለን ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ሞገስ ወንድሙ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ማሾ በመዝራት ከ15 ኩንታል በላይ ምርት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጣርማበር ወረዳ የዋንዛ በረት ቀበሌ አርሶ አደር ካሳሁን ተረፈ በበኩላቸው በአንድ ሄክታር መሬት የዘሩት ማሾ ሰብል ቡቃያው ያማረ በመሆኑ ከ30 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ  ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡ በዞኖቹ በ2010/11 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው መሬት 269 ሺህ 673 ኩንታል  ምርት ይጠበቃል። ማሾ ከቆላማ አየር ንብረት ከሚበቅሉ ጥራጥሬ ሰብሎች ውስጥ የሚመደብና ፍሬው በዋናነት ለምግብነት  የሚያገልግል ሰብል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም